ቀጥታ፡

የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ የካቲት1/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት መከላከያ ከመቀሌ ሰብዓ እንደርታ ፤ አራት ሰዓት ከ 30 ፌደራል ፖሊስ ከሊጉ መሪ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታሉ።

ነገ በድሬዳዋ ድሬዳዋ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጋር ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከነገ በስቲያ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ከ 30 ፌዴራል ማረሚያ ከከምባታ ዱራሜ አዲስ አበባ ላይ ሲጫወቱ ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከጎንደር ከተማ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት የሚጫወቱ ይሆናል።

በፕሪሚየር ሊጉ የቂርቆስና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቡድኖች ያደረጓቸውን አራት ጨዋታዎች ያሸነፉ ሲሆን በአንጻሩ ቡታጅራ ከተማና ጎንደር ከተማ ያደረጓቸውን አራት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል።

10 ክለቦች እየተሳተፉበት የሚገኘውን የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ ስምንት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን መቀሌ ሰብዓ እንደርታ በሰባት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ጎንደር ከተማና ቡታጅራ ከተማ ያለ ምንም ነጥብ በግብ እዳ ተበላልጠው ዘጠነኛ እና 10ኛ ደረጃን ይዘዋል።

በሌላ በኩል በሰባተኛው ሳምንት የሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ሙገር ሲሚንቶና አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ወላይታ ድቻና መዳወላቡ ዩንቨርሲቲ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዞን አምስት የቮሊቦል የክለቦች ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ በመሆኑ እንዲሁም በተደራራቢ ጨዋታዎች ምክንያት ለተወሰኑ ቡድኖች የእረፍት ጊዜ መስጠት ስላስፈለገ በሳምንቱ አንድ ጨዋታ ብቻ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ስምንት ቡድኖች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም