በቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ የካቲት 1/2011 በወላይታ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሁለተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ውድድሩ ከትናንት በስቲያ እንደተጀመረ ይታወሳል።
ዛሬ በውድድሩ የሶስተኛ ቀን ውሎ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በ48 ኪሎ ግራም ሴት የአዲስ አበባ ፖሊሷ ቤተልሄም ገዛኸኝ ከድሬዳዋ ከተማዋ ተወዳዳሪ ሀገሬ እማኙ በ54 ኪሎ ግራም ሴት የሰገን ክለብ ተወዳዳሪ የሆነቸው ሰናይት አሰፋ ከአዲስ አበባ ፖሊሷ ገነት ጸጋዬ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በ81 ኪሎ ግራም ወንድ የወላይታ ጦናው ጌታሁን ማዲቦ ከማራቶን ክለብ ተወዳዳሪው ተመስገን ምትኩ ጋር ይጫወታሉ።
ከፍጻሜ ውድድሮቹ በተጨማሪ ዛሬ በ52፣ በ56፣ 64፣ 69 እና 81 ኪሎ ግራም ወንድ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች እንደሚካሄዱም አመልክተዋል።
ከትናንት በስቲያ በተደረጉ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች አዲስ አበባ ፖሊስ በ51 እና 60 ኪሎ ግራም ሴት በማሸነፍ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱንና ፌዴራል ፖሊስ በ91 ኪሎ ግራም ወንድ የወርቅ ሜዳሊያ እንዳገኘም አስታውሰዋል።
ብሔራዊ የክለቦች ቦክስ ውድድር በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን የመጀመሪያው ውድድር ህዳር 2011 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ እንደተካሄደ ይታወሳል። ቀጣዮቹ ሁለት ውድድሮችም በጅግጅጋና አዲስ አበባ ይካሄዳሉ።
በቦክስ ውድድሮቹ የተገኘው አጠቃላይ ውጤት ተደምሮ በሁለቱም ጾታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦች የ2011 ዓ.ም የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚሆንም አስረድተዋል።
ሁለተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ነገ ፍጻሜውን ያገኛል።
በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከዘጠኝ ክለቦች የተወጣጡ 80 ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ነው።
በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ውድድሮቹ የሚካሄድባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።