በአዲስ አበባ ለሚገነባው የጊኒ ኤምባሲ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

111

አዲስ አበባ የካቲት 1/2011 ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና የጊኒው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ በአዲስ አበባ ለሚገነባው የጊኒ ኤምባሲ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት አቅራቢያ በሁለት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው የጊኒ ኤምባሲ ከኢትዮጵያ ባሻገር በጅቡቲ፣ በታንዛኒያ፣ በዩጋንዳ፣ በኬንያና በሶማሊያ ጊኒን የሚወክል አምባሳደር መቀመጫ ይሆናል።

ኤምባሲው የኢትዮጵያና ጊኒን ስትራቴጂካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁልፍ ሚና እንደሚኖረውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአፍሪካ አገራትን የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ ትብብር ለማጠናከረ ሁሉም የህብረቱ አባለ አገራት ዘመናዊ የኤምባሲ ፅህፈት ቤት በአዲስ አበባ ይኖራቸው ዘንድ የህንፃ መስሪያ ቦታዎችን በነፃ ሰጥቷል። 

በዚህም መሰረት በርካታዎቹ የራሳቸውን ህንፃ ገንብተዋል፤ ሌሎችም በመገንባት ላይ ናቸው።

የጊኒ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አልፋ ኮንዴ በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያና ጊኒ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ በጤና፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በግብርና ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶችን በትላንትናው እለት ተፈራርመዋል።

ሀገራቱ የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) በግንባር ቀደምትነት ከመሰረቱ አገራት መካከል ናቸው።

ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ በ32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይም ይገኛሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም