ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ መንገድ አስደናቂ ነው - ዶክተር መሐመድ ኢብራሂም

88

አዲስ አበባ የካቲት 1/2011 ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ መንገድ አስደናቂ ነው ሲሉ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን መስራች ዶክተር መሐመድ ኢብራሂም ተናገሩ።

ፋውንዴሽኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያከናውኑት ተግባር እንደሚደግፍም አክለዋል።

ዶክተር መሐመድ ኢብራሂም ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ሲነጋገሩ እንዳሉት "ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለው መንገድ አስደናቂ ነው"።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በእነዚህ ለውጦችና አፍሪካን እየገጠማት ባለው መሰናክል ላይ ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸውንም ጠቁመዋል።

ፋውንዴሽኑ በተለይ በአስተዳደርና በአፍሪካ ልማት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያካሄዱት ያለውን ተግባር እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ጠቃሚ አገር መሆኗን በመጠቆም።

ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2006 የተቋቋመ አህጉር አቀፍ ፋውንዴሽን ነው።

ፋውንዴሽኑ በዋናነት በአስተዳደር ላይ ትኩረቱን አድርጎ  የሚሰራ ሲሆን፤ በስልጣን ዘመናቸው ለውጥን ማስመዝገብ የቻሉ የአፍሪካ መሪዎችን ይሸልማል።

የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍም በ2017 ይህን ሽልማት ማግኘት ችለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም