ቀጥታ፡

ሰራዊቱ ህዝባዊ ባህሪውን ጠብቆ ለተጀመረው አገራዊ ለውጥ የድርሻውን ይወጣል-ሜጀር ጀኔራል መሃመድ ተሰማ

አዲስ አበባ ጥር 30/2011  የአገር መከላከያ ሰራዊት ህዝባዊ ባህሪውን ጠብቆ ለተጀመረው አገራዊ ለውጥ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ የሰራዊቱ ኢንዶክትርኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል መሃመድ ተሰማ ገለጹ

ሰባተኛው የአገር መከላከያ ሰራዊት ቀን  "ህገመንገስታዊ ታማኝነታችንንና ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን" በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የቤላ ክላስተር ሰራዊት አባላት አካባቢያቸውን በማጽዳት፣በተለያዩ ስፖርታዊና ኪነጥበባዊ  ክዋኔዎች በዓሉን አክብረዋል።

ሜጀር ጀኔራል መሃመድ ተሰማ በዚህን ወቅት እንዳሉት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰራዊቱን ህዝዊነትና አገራዊ ገድል ምስክሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሰራዊቱ ብሔርና ዘር የለውም፤ወገንተኝነቱም ለህገ-መንግስቱና ለህዝብ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሰራዊቱ በቀጣይም ይህን ባህሪውን ተላብሶ ተልዕኮውን አንደሚፈጽም ገልፀዋል።

በዓሉ ሲከበር ሰራዊቱ ለቆመለት ዓላማ በጽናት በመታገል እንደ አገር የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ቃል በመግባት መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉ ሰራዊቱ አባላት በበኩላቸው የህይወት መስዋትነት በመክፈል ጭምር አገርና ሰራዊቱ ህዝብን ከአደጋ እየተከላከለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሻለቃ ገዛሀኝ ስንታየሁ ሰራዊቱ ህዝብን ለመጠበቅ የሚከፍለው ዋጋ የህዝባዊነቱ ማሳያ አንደሆነ ይናገራሉ።

የበዓሉ መከበር ሰራዊቱ ግዳጁን ለመወጣት የሞራል ስንቅ እንደሚሰጠው የተናገሩት ደግሞ አስር አለቃ ሰላም ካሳዬ ናቸው።

ሰባተኛው የአገር መከላከያ ቀን የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም በአዳማ ስቴዲዬም በተለያዩ ዝግጅቶች በርካታ ህዝብ በተገኘበት ፍጻሜውን አንደሚያገኝ የወጣው መርሃ ግብር ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም