ለህብረቱ ጉባኤ ተሳታፊዎች አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል

134

አዲስ አበባ ጥር 30/2011 በአዲስ አበባ የተጀመረው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊ እንግዶች ድንገተኛ የጤና እክል ቢገጥማቸው የህክምና እርዳታ ለመስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት ማደረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዛሬ በተጀመረው 32ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ ከ40 በላይ የህብረቱ አባል አገራት መሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህም ሌላ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች፣ በርካታ ጋዜጠኞችና ሌሎች ተጋባዥ እንገዶች የጉባኤው ታዳሚ ይሆናሉ ተብሏል። 

እነዚህ እንግዶች  የጤና አክል ቢገጥማቸው ፈጣንና ጥራቱን የጠበቀ የህክምና እርዳታ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ነው በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ለኢዜአ የገለፁት።

ሚኒስቴሩ ከጉባኤው አስተባባሪ ኮሚቴ አንዱ በመሆኑ ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ አየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።   

በዚህም መሰረት አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ ባለው ቋሚ ክሊኒክ ሶስት እገዛ የሚያደርጉ ሃኪሞች በተጨማሪነት ተመድበዋል። ከዚህም ሌላ በቅጥር ግቢው ውስጥ  ሁለት ክሊኖኮች በጊዜያዊነት የተዘጋጁ ሲሆን አስር ሃኪሞችም ተመድበዋል።

በተጨማሪም ጉባኤውን ለመታደም የሚመጡ እንግዶች የሚገጥማቸውን ማንኛውንም ድንገተኛና መደበኛ ህመም ለመከታተል የተዘጋጁ ስድስት ሆስፒታሎች ዝግጁ እንዲሆኑ መደረጉንም ዶክተር ተገኔ ገልጸዋል።

ለዚህ ልዩ ተግባር የተመረጡት የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ አቤት ሆስፒታል፣ ኮሪያ ሆስፒታል፣ የመከላከያ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ላንድ ማርክ ሆስፒታልና ቤተል ቲቺንግ ሆስፒታል ናቸው።

በአዲሰ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ደግሞ የኢቦላ ምርመራ የሚካሄድበት ማዕከል መዘጋጀቱን የገለፁት ዶክተር ተገኔ፤ በተለይ በጉባኤው ለመሳተፍ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለሚመጡ እንግዶች ምርመራ እንደሚደረግ አክለዋል።

መሪዎቹ ሲወጡና ሲገቡም ለድንገተኛ አደጋ ዝግጁ የሆኑና አጅበው የሚሄዱ ተጠባባቂ አምቡላንሶች መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል። 

ከእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ጋር በመነጋገርም ሊያጋጥሙ የሚችሉ የእሳት አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል አምቡላንሶች ዝግጁ መሆናቸውን ዶክተር ተገኔ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም