ኢንዱስትሪዎች በብድር የወሰዱትን 292 ሚሊዮን ብር መክፈል አልቻሉም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዱስትሪዎች በብድር የወሰዱትን 292 ሚሊዮን ብር መክፈል አልቻሉም ተባለ
አዲስ አበባ ጥር 30/2011 በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማበረታታት ታስቦ ለኢንዱስትሪዎች በብድር የተሰጠ 292 ሚሊዮን ብር የሥራ ማስኬጃ ድጋፍ አልተመለሰም ተባለ።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የአገሪቱን ኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማበረታታት ግብዓትና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
በዚህም መሰረት ኢንዱስትሪዎቹ የሥራ ማስኬጃ ይሆናቸው ዘንድ በብድር የወሰዱትን ገንዘብ በወቅቱ እየመለሱ ባለመሆኑ ድርጅቱ በአሰራሩ ላይ እንቅፋት እየተፈጠረበት መሆኑን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ ተናግረዋል።
ድርጅቱ በስድስት ወር ጊዜ ለመሰብሰብ ከሰጠው 324 ሚሊዮን ብር የስራ ማስኬጃ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ በወቅቱ የተመለሰው 66 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው።
በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ለሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የኢንዱስትሪ ግብዓት ለማቅረብ፣ ለወጣቶች ስራ እድል ለመፍጠር እና ሌሎች ዘርፉን ለማበረታታት ለሚካሄዱ ተግባራት የሚያስፈልገውን ኃብት በአግባቡ ለመጠቀም እንቅፋት የፈጠረበት መሆኑን ገልፀዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ የተሰጣቸውን ብድር በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለመመለስ የገቡትን ውል ባለመጠበቃቸው በፍርድ ቤት ከሶ ለማስከፈል እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልፀዋል።
የገንዘብ ድጋፉን ከወሰዱት መካከል በቱርክ ባለኃብቶች የሚንቀሳቀሰው አይካ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፣ የድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፣ የኮምቦልቻ ቆዳ ፋብሪካ፣ ሀበሻ ታኒንግ እና ሀዋሳ ጨርቃጨርቅ ይገኙበታል።