የእግር ኳስ ተጫዋቾች ክፍያ መናር የክለቦችን ህልውና አደጋ ውስጥ እየጣለ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የእግር ኳስ ተጫዋቾች ክፍያ መናር የክለቦችን ህልውና አደጋ ውስጥ እየጣለ ነው ተባለ
አዲስ አበባ ጥር 30/2011 በኢትዮጵያ በየጊዜው እየናረ የመጣው የእግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች ክፍያ የክለቦችን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚጥል ነው ተባለ።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ብዙም ይነገርለት ያልነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች ወርሃዊ ክፍያ በአሁኑ ወቅት ከ250 ሺህ ብር በላይ ደርሷል።
ለዚህም ዋናው ምክንያት በክለቦች መካከል ያለው ያልተገባና ምክንያታዊ ያልሆነ ውድድር ነው ተብሏል።
በየዓመቱ እየጨመረ የመጣው የተጫዋቾች ክፍያ በሂደት የክለቦችን የፋይናንስ አቅም ቀውስ ውስጥ ሊጥል እንደሚችል ነው የተለያዩ ክለብ ኃላፊዎች ለኢዜአ የነገሩት።
በአሁኑ ወቅትም ለዘርፉ እድገት መሰረት የሆነውን ታዳጊ ተጫዋቾችን ለማፍራትና የስፖርት መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።
ክፍያው የስፖርቱን ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ፋይዳና የእድገት ደረጃ ያላገናዘበ ከመሆኑም በላይ ከተጨባጩ የሀገሪቱ ሁኔታ ጋርም የሚጣጣም አይደለም ተብሏል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የአዳማ እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበሴ መገርሳ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የተጫዎች ክፍያ በአንድ ዓመት ውስጥ እስከ 100 ፐርሰንት ጭማሪ አሳይቷል።
ክለባቸው ባለፈው ዓመት ለወንዶችና ለሴት ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች በየወሩ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል።
በዚህ ዓመት የተጫዋቾች ክፍያ በእጥፍ በሚባል ደረጃ በመጨመሩ አጠቃላይ የክለቡ ወርሃዊ የተጫዋቾች ክፍያ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እንደሚሆነ ነው አቶ አንበሴ የተናገሩት።
ክለቡ ይህን ያህል ደምወዝ እንዲከፍል የተገደደው የተጫዎች ክፍያ ከጊዜ ጊዜ እየናረ በመምጣቱ ተፎካካሪ ሆኖ በሊጉ ውስጥ ለመቆየት ሲል ነው ብለዋል።
ይህ የክለቦች ያልተገባ ፉክክር ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር ተመጣጣኝ ያልሆነና ለክለቦች ቀጣይነት ስጋት ነው ሲሉም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ እጅጉ በበኩላቸው የተጫዋቾች ክፍያ ከሀገሪቱ እግር ኳስ እድገት ጋር ተመጣጣኝ አይደለም ይላሉ።
ተገቢ ባልሆነ መንገድ እየናረ ያለውን የተጫዋቾች ክፍያ መልክ የሚያስይዝ አሰራር ሊበጅ እንደሚገባም ነው ሥራ አስኪያጁ የጠቆሙት።
ሁኔታውን ከወዲሁ መቆጣጠር ካልተቻለ ግን ክለቦች ላይ አስከመፍረስ የሚዘልቅ አደጋ ሊያከተል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ በቀለ ዋናው ቡድን የክለቡን ገንዘብ አሟጦ የሚወስድ በመሆኑ ለአንድ ሀገር እግር ኳስ እድግት ምስሶና መሰረት የሆነውን የታዳጊዎች ስልጠና እና የስፖርት መሰረተ ልማት እንዳይሰራ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።
ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ከተወሰነ ዓመት በኋላ ክለቦችን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከት ነው።
ሀገርን ወክሎ የሚወዳደረው የብሄራዊ ቡድን ተጫዎች ለማግኘትም አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ካሉት የፕሪሚየር ሊግ እግር ከኳስ ክለቦች መካከል አብዛኛዎቹ መንግስት በጀት የሚደጎሙ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ስንታየሁ ክፍያው በዚህ እያሻቀበ መሄዱ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብትን እንደሚጎዳው ገልፅ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም ክለቦች እርስ በእርሳቸው መክረው የጋራ መፍትሄ ሊያስቀምጡ ይገባልም ብለዋል።