ከ 30 የሚበልጡ የመድኃኒት አይነቶች በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
ከ 30 የሚበልጡ የመድኃኒት አይነቶች በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ተያዙ
አዲስ አበባ ጥር 30/2011 የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ከ 30 የሚበልጡ የመድኃኒት አይነቶች በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ መያዛቸውን ገለፀ።
ባለስልጣኑ ባለፉት ስድስት ወራት ህገ ወጥ መድሃኒቶችን ለመቆጣጠር የተከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት መግለጫ ሰጥቷል።
የባለስልጣኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ መለሰ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል በህገ ወጥ መንገድ ሊገቡ የነበሩ ከ 30 በላይ የመድኃኒት አይነቶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ከተያዙት መድሃኃኒቶች መካከል ለስንፈተ ወሲብ የሚያገለግል ቪ-ማክስ ፣ለጸጉር ማሳደጊያ ይውላል ተብሎ የሚሸጠው ሚኖግዚዲልና የካንሰር መድኃኒቶች ይገኙበታል።
መድኃኒቶቹ የተያዙት በመንገደኞች ሻንጣ ደብቆ ለማሳለፍ ሲሞከር መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
መድኃኒቶቹ በባለስልጣኑ ያልተመዘገቡ፣በአምራች ድርጅቶቹ የማይታወቁና አግባብነት ባለው የማጓጓዝና የማከማቻ ስርዓት ያላለፉ ሲሆኑ ለከፍተኛ የጤና ችግር የሚዳረጉ መሆናቸው ተረጋግጧል።
ሰውነትን ለመገንባት ይውላሉ የተባሉ ምግቦችም በቦሌ አለም አቅፍ ኤርፖርት በኩል በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብተው በስፖርት እቃ መሸጫ ሱቆችና ፣ የአካል ብቃት መስሪያ ቤቶች እየተሸጡ መሆኑንም ባለስልጣኑ ባደረገው ክትትል ማወቁን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉ አምስት ኬላዎች ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገው ቁጥጥር ጥራትና ደህንነታቸው ያልተጠበቀ 686 ቶን የተለያዩ ምግብና የምግብ ጥሬ ዕቃዎች ተይዘዋል።
ከ 680 ሊትር በላይ ዘይት ወደ አገር ውስጥ ሲጓጓዝ በመበላሻቱ እንዲሁም 1 ሚሊዮን 180 ሺህ ብር የሚያወጡ መድኃኒቶች፣የህክምና መሳሪያዎችና ኮስሞቲክሶች መስፈርቱን ባለሟሟላታቸው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓልም ብለዋል።
በባለስልጣኑ የመድኃኒት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ገዛኽኝ እንዳለ በበኩላቸው በገበያ ላይ በተደረገ ቅኝት ህገ ወጥ መድኃኒቶቹ በደላሎችና በማህበራዊ ሚዲያዎችና በድረ-ገጽ እንደሚሸጡ ተደርሶበታል ብለዋል።
ህገ ወጥ መድኃኒቶቹ የላብራቶሪ ፍተሻ፣ የመልካም አመራረት ስርዓትና የሰነድ ግምገማ ያልተካሄደባቸው እንዲሁም ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ መድኃኒቶቹ የሚያስከትሉትን ከፍተኛ የጤና ችግር ተገንዝቦ ምርቶቹን ከሃኪም ትዕዛዝ ውጪ እንዳይጠቀም በማለትም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።