ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያፀደቀቸውን የስደተኞች አዋጅ ኦክስፋም አደነቀ

አዲስ አበባ ጥር 30/2011  የኢትዮጵያ ስደተኞች አያያዝን ለማጠናከር ያወጣችውን አዋጅ ኦክስፋም የተሰኘው ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ  ድርጅት አደነቀ።

ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳናዊያንንና ኤርትራዊያንን ጨምሮ ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ የተለያዩ አገራት ስደተኞችን ታስተናግዳለች።

በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣው አዋጅ እነዚህ ስደተኞች ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩበት፣ ትምህርታቸውን የሚከታተሉበትና ሰርተው ኃብት የሚያፈሩበትን ጨምሮ የተለያዩ መብቶችን የሚያረጋግጥ ነው። 

በኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ ኦክስፋም ዳይክተር ሚስተር አፖሎ ንፎር የስደተኞች ችግርን መፍታት በሚቻልበት መንገድ ላይ ከሚመለከታቸው የተለያዩ አገራት ተወካዮች ጋር አዲስ አበባ ውስጥ መክረዋል።

በዚሁ ወቅት ዳይክተሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ የስደተኞች አዋጅ በማውጣት መብታቸውን ለማክበር እያከናወነች ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው።

በስደተኞች ላይ የሚደርሰውን በደል ለማስቀረትና የሰብዓዊ መብታቸውን ለማስከበር የሌሎች አገራት መንግስታትም የበለጠ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ስደተኞች እንደማንኛውም ዜጋ የመንቀሳቀስ እና ኃብት የማፍራት መብት እንዳላቸው የፓን አፍሪካ ኦክስፋም ዳይሬክተሩ አክለዋል።

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ አገራት ይህንን መብት ለማስከበር ውጤታማ ተግባር እያከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ዩጋንዳንና ኢትዮጵያን  አብነት አድርገው አንስተዋል።

የኡጋንዳ መንግስት  በአገሪቱ ለሚገኙት ስደተኞች መሬት እስከ መስጠት የደረሰ አዎንታዊ ተግባር ማከናወኑን ጠቅሰው ሌሎች አገራትም የዩጋንዳን ምሳሌ መከተል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተመሳሳይ እንደ ሚሊዮን የሚጠጋ ስደተኞችን ያስጠለለቸው ኢትዮጵያ የስደተኞችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ያወጣችው ህግ ለሌሎች አገራትም ምሳሌ ሊሆን የሚችል እንደሆነ  በኢትዮጵያ ኦክስፋም ዳይሬክተር አቶ ገዘህኝ ከበደ አስታውቀዋል።

የዜጎችንና ስደተኞችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል ዝርዝር የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊ እንደሆነ አዋጁ በወጣበት ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

አዋጁ ወደኢትዮጵያ የሚገቡት ስደተኞች በአግባቡና በትክክል እንዲለዩ፣ የሚኖሩበት ሁኔታ እንዲታወቅ፣ ሲወጡ እንዴት እንደሚወጡና የሚያፈሩትን ንብረት የሚያስተዳድሩበትን ስርዓት በግልጽ ለማወቅ ያግዛል ተብሏል።

ይህም በስደተኝነት ሰበብ የሚፈፀሙ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ያስችላል የሚል እምነት ተጥሎበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም