በጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር ኤርትራውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር ኤርትራውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ ጥር 29/2011 በመጪው እሁድ በሚካሄደው የጃንሜዳ ኢንተርናሽል አገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር ኤርትራውን አትሌቶች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ።
የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ እንደተናገሩት፤ ውድድሩ በአዋቂ አትሌቶች፣ በወጣትና በድብልቅ ሪሌ ይካሄዳል።
በውድድሩም ከኤርትራ የሚመጡ አትሌቶች በእያንዳንዱ ምድብ አንድ ወይም ሁለት አትሌቶች እንደሚካፈሉ ነው የገለጹት።
ከኤርትራውያን አትሌቶች በተጨማሪ ከሱዳንና ከጅቡቲ በውድድሩ ለመካፈል የሚመጡ አትሌቶች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
በዚህ ውድድር በወጣቶች ምድብ በሁለቱም ጾታ ከአንደኛ እስከ ስድስትኛ ሆነው የሚያጠናቅቁና በአዋቂ ደግሞ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ የሚወጡ አትሌቶች በመጪው መጋቢት ወር በዴንማርክ በሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር አገራቸውን ወክለው ይካፈላሉ ተብሏል።
በጃንሜዳ ኢንተርናሽል አገር አቋራጭ ሩጫ ውድድር እድሜያቸው 16 እና 17 ዓመት የሆናቸው በወጣት ምድብ የሚወዳደሩ ይሆናል።
እንዲሁም ከ18 እስከ 19 ዓመት የሆኑ ደግሞ በወጣትና በአዋቂው ምድብ የመወዳደር እድል ያላቸው ሲሆን እድሜቸው ከ20 ዓመት በላይ የሆኑት ደግሞ በአዋቂ አትሌቶች ምድብ የሚወዳደሩ ይሆናል።
በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ የሚወጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት የሚሰጣቸው ሲሆን ከአንድ እስከ ሶስት ሆነው ለሚጨርሱ አትሌቶች ደግሞ ከገንዘብ ሽልማቱ በተጨማሪ የሜዳሊያ ሽልማት የሚያገኙ ይሆናል።
ለ36ኛ ጊዜ በሚካሄደው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ውድድር የሚደረግ ሲሆን በውድድሩም ከክለቦች፣ ከማሰልጠኛ ማዕከላት ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 300 ሴትና 616 ወንድ አትሌቶች ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል።