ቀጥታ፡

ግንቦት 20 ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ አስችሏታል--- አቶ ጌታቸው ረዳ

መቀሌ ግንቦት 20/2010 " ግንቦት 20 ኢትዮጵያ ከመበታተን አደጋ ወጥታ በፈጣን የኢኮኖሚ ጉዞ እንድትጓዝ ያስቻለ ታላቅ በዓል ነው" ሲሉ የህወሓት/ኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። 27ኛው የግንቦት 20 በዓል ትናንት በመቀሌ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ነባር የህወሓት ታጋዮች፣ የከተማው የህዝብ ተወካዮች፣ ምሁራንና ሌሎችም  ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በፓናል ውይይት ተከብሯል። አቶ ጌታቸው " የግንቦት ሃያ ስኬቶችና ስጋቶች" በሚል ርዕስ ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ ላይ እንዳሉት፣የግንቦት ሃያ ድል በዓል ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከመበታተን የታደጋት ታላቅ ቀን ነው። በህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን መጠራጠርና ስጋት እንዲወገድ ማስቻሉንም ተናግረዋል። በዓሉ ህገ መንግስታዊ ዋስትናን በማረጋገጥ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በመፈቃቀድና በእኩልነት የሚስተናገዱባት የብዙሃነት ሃገር እንድትሆን እንዳስቻለም አመልክተዋል። ግንቦት 20 የህብረ ብሔራዊነት ባህሪ ያለውን የህዝቦችን አደረጃጀትና ራስን በራስ የማስተዳደር ስርዓትን በመዘርጋት መነሻውም መድረሻውም የሃገሪቱ ህልውና በጠንካራ የህዝቦች አንድነት ላይ እንዲመሰረት አስችሏል። ከግንቦት ሃያ የድል በዓል ትሩፋቶች መካከል በህዝቦች የጋራ ራዕይ፣ አስተሳሰብና ግብ ተመስርቶ ሃገርን የጋራ ማድረግ እንደሚገኝበት ነው አቶ ጌታቸው የገለጹት። በሃገሪቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሰረተ ልማት ስራዎችን በማከናወን ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት  ኋላቀርነት ወጥታ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገታቸው ከሚጠቀሱ ጥቂት ሃገራት መካከል  እንድትጠቀስ ያደረገው የግንቦት ሃያ የድል ስኬት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ከግንቦት ሃያ የድል በዓል ማግስት ጸድቆ ስራ ላይ የዋለው ህገ መንግስት የኃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ብዙሃነትን በግልጽ ያስቀመጠና ህዝቦች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው እንዲወስኑ ያልተሸራረፈ መብት ያጎናጸፈ መሆኑን ተናግረዋል። ሆኖም የኪራይ ሰብሳቢት ተግባርና አመለካከት ዋንኛ ስጋቶችና የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናትም ሳይቀር በዚህ ተግባር እየተፈተኑ መሆናቸውን የተናገሩት  ደግሞ የህወሓት መስራች ታጋይ አምባሳደር ስዩም መስፍን ናቸው። አሁን እየታየ ባለው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር እየተገነቡ ያሉ የዲሞክራሲ ተቋማትን ማስቀጠል ቀርቶ ሙሉ በሙሉ የሚጠፉበት  አጋጣሚ ሊከሰት እንደሚችል ነው አምባሳደር ስዩም ስጋታቸውን የገለጹት። ከዚህ ችግር በመላቀቅ ከድህነት ለመውጣት አመራሩ መትጋት እንደሚጠበቅበት ጠቁመው " እኛ ራሳችንን ለለውጥና ለአዳዲስ አሰራሮች ዝግጁ ማድረግ ይጠይቀናል" ብለዋል፡፡ በተለይ ለስኬታማ  ሰላምና የህግ ልዕልና መረጋገጥ  መስራት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል። የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ መስራች ታጋይ ህላዌ ዮሴፍ  የትግሉ መነሻዎችን አስመልክተው ባቀረቡት ጽሁፍ "ከግንቦት ሃያ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩ የተለያዩ ጭቆናዎች ምክንያት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች በተናጠልና በተደራጀ መልክ ሲታገሉ ቆይተዋል" ብለዋል። ኢህአዴግን ካታገሉት ዋነኛ የህዝብ ጉዳዮች መካከል  የዲሞክራሲ መብቶች፣ የመሬት ባለቤትነት፣ የሰላምና የልማት ጥያቄዎች  እንደነበሩ አስታውሰዋል። ኢህአዴግ ደርግን ደምስሶ ለድል እንዲበቃ ካስቻሉት ልዩ ባህሪያት፣ ግልጽ ስትራተጂ የተከተለ፣ ራሱን በህዝብ ውስጥ ያኖረና ለህዝብ ልዕልና የቆመ እንዲሁም በሂደት ከድክመቱና ጥንካሬው እየተማረ የሄደ ድርጅት በመሆኑ እንደነበር ታጋይ ህላዌ አውስተዋል። "አሁንም ኢህአዴግ ሲከተላቸው የቆዩ መርሆዎችን በማጠናከር ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን መመልከት፣ ድክመቱንም እንደትናንቱ ማረምና ማስተካከል ከቻለ የልማትና የዲሞክራሲ ዓላማዎቹ እንደሚቀጥሉ የጸና እምነት አለኝ "ብለዋል። የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎችና አደጋዎች፣ በኢህአዴግ የትጥቅ ትግልና ዛሬ ባለው አቋሙ ላይ ያሉበትን ችግሮች ያተኮሩ ጥያቄዎች አንስተው በመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም