መሬታቸውን በግፍ የተቀሙት አርሶ አደር ፍትህ አገኙ

174

አዲስ አበባ ጥር 29/2011 በ"ግፍ ከመሬታቸው" የተፈናቀሉትና ለጎዳና ተዳዳሪነት የተዳረጉት የ48 ዓመቷ አርሶ አደር ወይዘሮ ሙሉ ደምሴ ከ13 ዓመታት እንግልት በኋላ ፍትህ አገኙ።

ወይዘሮ ሙሉ መሬታቸው በተመለሰበት ወቅት ወደ ተወለዱበት ቀዬ በማመራት ከጎረቤት ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ተቃቅፈው የደስታ እንባ አንብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከወራት በፊት ባዘጋጀው ልዩ የምርመራ ዘገባ መሬታቸውን በግፍ በመቀማታቸው የጎዳና ተዳዳሪ ለመሆን መገደዳቸውን የሚያትት ሰፊ ዘገባ አውጥቷል።

በዚህ መሰረትም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባደረገው ሰፊ የማጣራት ሥራ ለወይዘሮ ሙሉ በልዋጭ የተሰጠ መሬት አለመኖሩን አረጋግጧል።

https://www.youtube.com/watch?v=H3LsilraqyA&t=36s

መሬታቸውን በግፍ የተቀሙት አርሶ አደር ፍትህ አገኙ

ተቋሙ ጉዳዩን እስከመጨረሻው ሲከታተል ቆይቶ አርሶ አደሯ በግፍ የተቀሙትን መሬት ከ13 ዓመታት በኋላ ሲመለስላቸው በስፍራው ተገኝቶ ዘግቧል።

ወይዘሮ ሙሉ ፍትህ በማጣታቸው ሳቢያ ከትውልድ አካባቢያቸው ከአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ደርባ ጉለሌ በሬሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ነው የተሰደዱት።

ከአባታቸው የወረሱትን አምስት ሄክታር መሬት በአንድ ግለሰብ በመቀማታቸው ከስምንት ዓመታት በላይ ለጎዳና ተዳዳሪነትና ለተመጽዋችነት ተዳርገዋል።

ወይዘሮ ሙሉ ዛሬ ላይ ያ ሁሉ አልፎ ከ13 ዓመታት በኋላ በ"ግፍ የተቀሙትን መሬት" የሱሉልታ ወረዳ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት መልሶላቸዋል።

ከ13 ዓመታት እንግልት በኋላ ፍትህ ያገኙት አርሶ አደር ወ/ሮ ሙሉ ደምሴ

ወይዘሮ ሙሉ ደምሴ በሰጡት አስተያየት "በጣም ነው ደስ ያለኝ። ከነ ቤተሰቦቼ መጥቼ መሬቴን መቀበሌ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ዘመዶቼ ያልሰሩልኝን ነው የሰራችሁልኝእስከ ዛሬ ድረስ 13 ዓመታት ሙሉ ከአገኘሁ በልቼ ካጣሁ አድሬ ያለሁበት ሸራ ቤት አይታችኋል ያ ሁሉ አልፎ አሁን ሰው እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ እድሜ ለእናንተ ኑሩልኝ መንግስትም ይኑር ሁላችሁም ዜና አገልግሎቶች ኑሩልኝ በጣም አመሰግናለሁ።"

የወይዘሮ ሙሉ ልጆች ወርቄ ዳባ እና ፤ መሬታቸው በመመለሱ የተበታተነው ቤተሰብ ዳግም በአንድነት እንዲኖር በር የከፈተ በመሆኑ ደስታቸው ወደር እንደሌለው ነው የተናገሩት። 

ወርቄ ዳባ " በጣም ደስ ብሎኛል 13 ዓመት ሙሉ እናቴ ጎዳና ላይ ናት እኛም ተበታትነን ነበር። ዛሬ በመሰብሰባችን በጣም ደስ ብሎኛል። ዘመዶቻችን ብዙ ናቸው ግን ምንም አላደረጉልንም። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን በጣም አመሰግናለሁ ምክንያቱም የእኛ ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ነው። እናቴም ከአሁን በኋላ አንድ ቤት ትቀመጣለች። ቤተሰቦቼ እህቶቼ ወንድሞቼ ሁሉ አንድ ቦታ ይቀመጣሉ በጣም ደስ ብሎኛል።”

ጌቱ ዳባ በበኩሉ"በመጀመሪያ እግዛብሄር ይመሰገን እላለሁ እናንተን ሰለ ሰጠን።ያልታሰበ ነገር ነው ተስፋ ቆርጠን ነበር በነገራችን ላይ። ብዙ ነገር ሆነናል። እናታችንም ብዙ ነገር ሆናለች። አቅም ስናጣ የምንበላው ስናጣ በዚህ መሬት ልጆቹን እያስተማረ እኛ ሳንማር ነው ያለነው ፤በጣም ነው የማመሰግነው።"

የወይዘሮ ሙሉ ደምሴ ልጆች ከግራ ወደ ቀኝ ወርቄ ዳባ፣ ጌቱ ዳባ እና ያአብስራ ዳባ

የወይዘሮ ሙሉ ደምሴ ልጅ የ8 ዓመት ህጻን እና የአንደኛ ክፍል ተማሪ ያአብስራ ዳባ፤

"ፊቴ በብርድ ተበላሽቷል። ከዚህ በኋላ ግን ቤትም ስለሚሰጠን ብርድ አይነካንም። ለእናቴ ቤት ሰርቼ ሁሉን ነገር አሟልቼ እሱን ነው የምፈልገው።እናቴ ከዚህ በፊት በጣም ትናደዳለች አሁን ግን ደስ ብሏታል።"

የሱሉልታ ወረዳ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ጉዳዩን በጥልቀት ሲመረምር ቆይቶ በአሮሚያ ክልል በ1999 ዓ.ም የወጣን የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር  መመሪያ መሰረት አድርጎ መሬቱን መመለሱን ነው የገለጸው።

በመመሪያ ላይ በተጠቀሰው መሰረት አንድ ሰው መሬት ሊያገኝባቸው ከሚችልባቸው ምክንያቶች በመንግስት ምሪት፣ በስጦታ እና በውርስ የሚሉት ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው።

በመሆኑም የወይዘሮ ሙሉን "መሬት ቀምተዋል" የተባሉትን ግለሰብ አቶ መስፍን በረዳ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የመሬቱን የይዞታ ማረጋገጫ በባለቤታቸው ስም በማውጣት ከተጠቀሱት የመሬት ማግኛ መንገዶች ውጪ የመሬቱ ባለቤት ሆነው መቆየታቸውን ለመረዳት መቻሉን አስተዳደሩ ይገልጻል።

ስለዚህ የሱሉልታ ወረዳ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት አቶ መስፍን በረዳ በባለቤታቸው ስም ያወጡት የ"ይዞታ" ማረጋገጫ ህገ ወጥ መሆኑን በማጣራት እንዲሰረዝ እና ህጋዊ ባለቤት ለሆኑት ለወይዘሮ ሙሉ ደምሴ የመሬት "ይዞታ" ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው አድርጓል።

የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛው ታደሰ፤ የመሬት አጠቃቀም መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ ግለሰቡ በህገ ወጥ መንገድ የመሬት ባለቤት ሆኖ መቆየቱን ይናገራሉ።

ከግራ ወደ ቀኝ የሱሉልታ ወረዳ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግዛው ታደሰ እና ወ/ሮ ሙሉ ደምሴን በነፃ የጥብቅና አገልግሎት የሰጡት አቶ ረጀብ ኡስማን

" በወረዳችን እየተሰራ ያለ የሁለተኛ ዙር የመሬት ልኬት እንዳለ ይታወቃል።በዚያ ሰበብ ነው ይሄንን የሰማነው ስንሰማም መሬቷን ተቀምታለች በሷ ስም ግብር ይገበራል።በእሷ የሚገበረው ለይስሙላ እንጂ ገንዘቡን የሚሰጠው አቶ መስፍን እንደሆነ መረጃውን አግኝተናል። እሱ ላይ ቆመን ነው ይሄንን ነገር ልንሰራ የቻልነው። እሱንም ቢሮ ጠርተን አነጋግረን ነበር። መረጃ ለመስጠትም ብዙ ፍቃደኛ አይደለም።እዚህ መሬት ላይ ሁለት ደብተር አለ በአቶ መስፍን በረዳ ስም ሳይሆን በባለቤታቸው ስም ደብተር ተሰርቷል። ይሄንን እንዴት አሰራክ ብንል ፍርድ ቤቱ ሰለወሰነልኝ ይሄን መሬት ወደ ራሴ አዙሬያለሁ አለ። አንድ ሊታወቅ የሚገባው ነገር አለ በገጠር መሬት አጠቃቀም ላይ የመሬት ደብተር የሚወጣው በወንድ ስም ነው።በአባወራ ነው። በባለቤት ስም አይሰራም እሱ ግን ይሄን ተንኮል ሰለ አሰበ የራሱ መሬት ስላለው በእሷ ስም ነው ያሰወጣው።"

ይህ በመሆኑ የወረዳው መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት፤ መሬቱን ለወይዘሮ ሙሉ ደምሴ መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት "የመሬቱ ባለቤት" መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ሰቷቸዋል።

"የሚፈቅድልን የመሬት አስተዳደር መመሪያ አለ ያንን መመሪያ ተንተርሰን የአካባቢው ሽማግሌዎች የሚሉትን ነገር ከወሰድን በኋላ አንዱን ደብተር ሰርዘን ለመጀመሪያው ባለቤት ሰተን ያንን መሰረዛችንን ደብዳቤ ሰተን እሱን ማሳወቅ ነው ለሴትየዋ ደግሞ በደብዳቤ ማሳወቅ ነው።መሬቱ ራሱ እኮ የአባታቸው መሬት ነው።የአባታቸውን መሬት ወርሶ እኮ ነው ወደ ደብተር ቀይሮ ሲጠቀምበት የነበረው። የእኩልም ሰተው ነበር ሲያሳርሱ የነበረው አሁን ያንን እኩል ማረስ ትቶ የራሴ ነው ወደ ሚል የመጣው እንጂ አሁን ይሄ መሬት የሷ ነው።"

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከወራት በፊት ያወጣውን መረጃ በማህበራዊ ድረ ገጽ ተመልክቶ ወይዘሮ ሙሉ ደምሴን በነፃ የጥብቅና አገልግሎት ለመስጠት ወደ ተቋሙ የመጣው ጠበቃ አቶ ረጀብ ኡስማን የመሬት አስተዳደሩ የሰጠው አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ።

"መሬት አስተዳደር የድርሻውን እየተወጣ ነው።አሁን ቀሪው ምን ይሆናል የሚለው ወይዘሮ ሙሉ ከ13 ዓመት በላይ ይሄን መሬት አጥታ ሳትጠቀምበት ሌላ ሰው ያለ አግባብ ከህግ ውጪ ሲጠቀምበት ነበር። በህገ ወጥ መንገድ መሬቱን ሲጠቀምበት የነበረው ወገን  ካሳ እንዲከፈላት እሷም ተመልሳ እንድትቋቋም የወደፊት የፍርድ ቤት ሂደቱን የምናደርገው ። ከአሁን በኋላም የወይዘሮ ሙሉ ጠበቃ ሆኜ በአሁኑ ሂደት ያለውን የካሳ ጥያቄ የምንቀጥል ይሆናል። እስከ መጨረሻም ደግሞ በእናንተ በኩል የተደረገው ድጋፍ ጉዳዩን ጎት ጉታችሁ ተከታትላችሁ አውጥታችሁ ለዚህ አብቅታችኋል።ይሄ ለወደፊት አብረን በምንሰራው ስራ ስኬት ላይ እንደርሳለን ብዮ እጠብቃለሁ።የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃውን እንዳገኘ በራሱ ተነሳሽነት ብዙ ጥረት አድርጎ በመስራቱ በጣም ምስጋና ይገባዋል።"

የሱሉልታ ወረዳ የአቃቢ ህግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡርጌሳ ፀጋዬ

የሱሉልታ ወረዳ የአቃቢ ህግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡርጌሳ ፀጋዬ በበኩላቸው፤ በወረዳው በመሬት ዙሪያ የወይዘሮ ሙሉ ደምሴን ጨምሮ ሌሎች ፍትህ የተጓደለባቸውን ሰዎች ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግ ተጨባጭ ስራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

"እኛ በወንጀል በኩል አጣርተን ይሄን ነገር ለህግ ለማቅረብ እንሞክራለን።የእርሳቸው ብቻ አይደለም ብዙ ነገሮች አሉ።ብዙ ማስረጃ ይዘናል። ሀብት እና ጉልበት ያላቸው ሰዎች የገጠር መሬት አቅም ከሌላቸው እየተቀበሉ ነው በሌላ መንገድ ሰለዚህ እኛም ከዚህ በኋላ ከእነሱ ጋር ሆነን በወንጀልም በፍትሐ ብሄርም አቅም የሌላቸውን ራሱ ጠበቃ መግዛት የማይችሉትን አቃቢ ህግ አቁመን በነፃ ልንከራከርላቸው ጀምረናል።"

ወይዘሮ ሙሉ መሬታቸው ይመለስላቸው እንጂ ቤት ለመስሪያ የሚሆን ገንዘብም ሆነ መሬታቸውን በወሰደባቸው ግለሰብ የደህንነት ስጋት ስላለባቸው ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ለመኖር ባለመቻላቸው አሁንም ጎዳና ላይ ከላስቲክ ሸራ በተሰራች ቤታቸው ከህፃናት ልጆቻቸው ጋር እየኖሩ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም