የተተኪዎች አትሌቲክስ ውድድር በኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የተተኪዎች አትሌቲክስ ውድድር በኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ግንቦት 20/2010 ስድስተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቋል። ከግንቦት 15 ቀን ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአሰላ አረንጓዴው ስታዴየም ሲካሄድ የሰነበተው ውድድር በድምቀት ተጠናቋል። ለአሰላና አካባቢዋ ነዋሪዎች ትልቅ ድምቀት ፈጥሮ የነበረው ውድድር በኦሮሚያ ክልል በ325 ነጥብ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቋል። በውድድሩ ከጋምቤላ ክልል በስተቀር ስምንት ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተሳተፉ ሲሆን ከ34 ክለቦችና ተቋማት የተውጣጡ ከ1 ሺህ 100 በላይ አትሌቶች ተካፍለዋል። በዚህ ውድድር በ200 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው በአትሌቲክስ ስፖርት እየጎላ የመጣው ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ ነው። መከላከያ ስፖርት ክለብ ደግሞ በ149 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቅቅ ችሏል። በውድድሩ ማጠናቀቂያ ከነበሩ ጨዋታዎች መካከል አምስት ሺህ ሜትር የወንዶችን ውድድር፣ 1 ሺህ 500 ሜትር በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም የሴቶች ሶስት ሺህ ሜትር ውድድሮች ተጠባቂ ነበሩ። በአምስት ሺህ ሜትር የወንዶችን የፍጻሜ ውድድር አትሌት ጥላሁን ኃይሌ ከሐዋሳ ከነማ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል። ኦሮሚያን ወክሎ የተወዳደረው ሚልኬሳ መንገሻ ደግሞ ሁለተኛ ሲሆን፤ አንተንአየሁ ዳኛቸው ከመከላከያ ሶስተኛ ደረጃን ማግኘት ችሏል። በወንዶች የ1 ሺህ 500 ሜትር ብርሃኑ ሶሬሳ ከኦሮሚያ ክልል አንደኛ ሆኗል። አማራ ክልልን ወክሎ የተወዳደረው መለሰ ንብረት ሁለተኛ ሲወጣ፤ ከበደ እንዳለ ከኦሮሚያ የሶስተኝነት ደረጃን አግኝቷል። በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር ደግሞ ድንቄ ፍርዴሳ ከኦሮሚያ ክልል አንደኛ አልማዝ ሳሙኤል እና ብሪ አበራ ከትራንስ ኢትዮጵያ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በሶስት ሺህ ሜትር ሴቶች ጽጌ ገብረሰላማ ከትራንስ ኢትዮጵያ፣ ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር ከጉና፣ አበራሽ ማስቦ ከሱር ኮንስትራክሽን ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። በዚህ ሻምፒዮና በመካከለኛና በረጅም ርቀቶች አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁ አትሌቶች በመጪው ሐምሌ በፊንላንድ በሚካሄደው የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚካፈሉ ሲሆን ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ደግሞ በተጠባባቂነት የሚያዙ ይሆናል።