የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቀን ከኤርትራ ጋር ከተፈጠረው ሰላም ማግስት ከምሽግ ውጭ ይከበራል-የሰሜን እዝ ኮማንድ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቀን ከኤርትራ ጋር ከተፈጠረው ሰላም ማግስት ከምሽግ ውጭ ይከበራል-የሰሜን እዝ ኮማንድ
ሽሬ እንዳስላሴ ጥር 29/2011 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቀን በኢትዮጵያና በኤርትራ ከተፈጠረው ሰላም ማግስት ከምሽግ ውጭ እንደሚከበር የሰሜን እዝ ኮማንድ አባላት ገለጹ።
በዓሉ "ህገመንግስታዊ ታማኝነታችንና ህዝባዊ ባህሪያችን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥል!" በሚል መሪ ቃል ሰባተኛው የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ቀን እየተከበረ ነው።
በሰሜን ምዕራብ ዞን ሸረ እንዳሥላሴ ከተማ እየተከበረ የሚገኘውን ቀን በዓል አስመልክተው የእዙ ኮማንድ አባላት ትናንት ምሽት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የሰሜን እዝ ምክትል አዛዥና የሰው ሃብት ልማት ኃላፊ ብርጋዲዬር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነና የእዙ ምክትል አዛዥና የሎጂስቲክስ ኃላፊ ብርጋዲዬር ጄኔራል ከድር አራርሳ እንደገለጹት የዘንድሮው የመከላከያ ቀን በዓል በኢትዮጵያና በኤርትራ ከተፈጠረው ሰላም ማግስት ከምሽግ ውጭ ያለ ስጋት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል።
በዓሉ የሁለቱ አገሮች ሰራዊት በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር እንደሚያከብሩት ብርጋዲዬር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር ተናግረዋል።
ሰራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የእርከን ስራዎች በማከናወን ፣ጧሪ የሌላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በመርዳት፣ ደም በመለገስና በስፖርት ውድድሮች ሲከበር መቆየቱን አስታውቀዋል።
ሰራዊቱ ሪፎርም እያደረገ ባለበት ወቅት በዓሉ መከበሩ ሰራዊቱ ለህዝቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማጠናከር እንደሚያስችለው ተናግረዋል።
የእዙ ምክትል አዛዥና የሎጂስቲክስ ኃላፊ ብርጋዲዬር ጀኔራል ከድር አራርሳ በበኩላቸው ሰራዊቱ እንደ መከላከያ ሰራዊት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከህዝብ ቅራኔ ሳይኖረው በፍቅር የተጓዘና ከግዳጁ በተጨማሪ የህዝቡ የልማት አጋር በመሆን ህዝባዊ ወገንተኝነቱ በተግባር እያረጋገጠ የመጣ ህዝባዊ ሰራዊት መሆኑን አመልክተዋል።
ሰራዊቱ ከውጭ ይሁን ከውስጥ የሚቃጣ ማንኛው ጥቃት የመከላከል ብቃቱ በአስተማማኝ ደረጃ እንደሚገኝም ብርጋዲዬር ጄኔራል ከድር ገልጸዋል።
በእዝ ደረጃ ከዛሬ ጀምሮ በፓናል ውይይት የሚከበረው በዓል የተሻለ ስራ ላከናወኑ የሰራዊት አባላት ማዕረግ የመስጠት፣በክብር የሚሸኙ አባላት ሽኝትና ወታደራዊ ትርኢቶች እንደሚካሄዱ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
ሰባተኛው የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ቀን በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ የካቲት 7/2011 በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ይከበራል።