ተፈናቃዮች ወደ ዴቻ ወረዳ ለመመለስ ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
ተፈናቃዮች ወደ ዴቻ ወረዳ ለመመለስ ጠየቁ
ሆሳዕና ጥር 29/2011 ከካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ የተፈናቀሉ የከምባታ ጠምባሮ ዞን ተወላጆች ወደነበሩበት ለመመለስ ጠየቁ፡፡
ተፈናቃዮቹ በ1996 በከምባታ ጠምባሮ ዞን በተከሰተው ድርቅ ወደ ካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ በሰፈራ ፕሮግራም የሄዱ ናቸው ።
ተፈናቃዮቹ እንዳሉት በአካባቢው በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ለመመለስ መገደዳቸውንና አሁን በአካባቢው ሰላም በመስፈኑ ኑሮአቸውን ዳግም በዚያ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቀዋል።
ለዚህም መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
ከከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ አንገላ ሠፈራ ጣቢያ ተፈናቅለው የመጡት አቶ ማርቆስ ጫኪሶ ከካፋ ሕዝብ ጋር በፍቅር በመኖር ንብረት እንዳፈሩ ይናገራሉ፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ ሰው አክባሪና እንግዳ ተቀባይ እንደሆነ ገልጸው፣እንደ ቀድሞ ከሕዝቡ ጋር በሰላም መኖር እንፈልጋለን ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
''መንግሥት ሰርተን እንድንኖርና ራሳችንን እንድንችል ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ወደ ሥፍራው ልኮናል''ያሉት ደግሞ ከዴቻ ወረዳ ገነት ቀበሌ ተፈናቅለው የመጡት አቶ ተረፈ አየነው ናቸው፡፡
''አሁንም ቢሆን ወደ ቀያችን ተመልሰን ሰርተን መለወጥና በሰላም ከማህበረሰቡ ጋር መኖር እንፈልጋለን'' ሲሉም ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
የከምባታ ጠንባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ታከለ ነጫ ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋም ከደቡብ ክልል መንግሥትና ከካፋ ዞን አስተዳደር ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከካፋ ዞን ለተፈናቀሉ የብሄሩ ተወላጆች አስተዳደሩና ሕዝቡ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት ዋና አስተዳደሪው፣የዞኑ አስተዳደር የአካባቢውን ሰላም በማረጋጋት ተፈናቃዮቹን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ሙሉ ፈቃደኛ ነው ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹን ለመርዳት በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው ተፈናቃዮቹን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከአጎራባች ዞኖች ጋር ጭምር እየሰራን ነው ብለዋል።
ወደ ከምባታ ጠምባሮ ዞን የተመለሱ ተፈናቃዮች 30 ሺህ እንደሚደርሱ ከዞኑ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።