ቀጥታ፡

ቤተ እምነቶችን ማቃጠልና ማውደም በሁሉም ሐይማኖቶች በፅኑ የሚወገዝ ተግባር ነው

አዲስ አበባ ጥር 28/2011 በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ የተፈፀመው መስጊዶችን የማቃጠልና የማውደም ተግባር የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ አወገዘ።

''ቤተ እምነቶችን ማቃጠልና ማውደም በሁሉም ሐይማኖቶች በፅኑ የሚወገዝ ተግባር ነው'' ብሏል፡፡

የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የተፈጠረው ችግር በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም ገልጿል።

''በየትኛውም የሐይማኖት አስተምህሮ ፍፁም ተቀባይነት የሌለውና የሚኮነን ድርጊት ነው'' ያለው ጉባዔው በእምነትና በአምልኮ ሥፍራዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ማንኛውም አካልም ሆነ ግለሰብ ድርጊቱ ኃጢአት እንደሆነ መገንዘብ እንዳለበት አስታውቋል። 

''በማንኛውም የእምነት ተቋም የሚፈፀም ይህን መሠል ተግባር፣ በአገራችን ለዘመናት በሠላምና በመከባበር ጠንካራ አብሮነትን ገንብተው በሚኖሩ የእስልምናና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የተቃጣ ክፉ ድርጊት በመሆኑ ዜጎች በፅናት ሊቃወሙት ይገባል'' ብሏል።

ድርጊቱን የፈፀሙ አካላት በህግ እንዲጠየቁ እንዲሁም መንግስት በቀጣይም ችግሮች እንዳይከሰቱ ተገቢውን ጥበቃና ሕግን የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጉባዔው በአጽንኦት ጠይቋል።

የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት በመፍታትና የተቃጠሉትን መስጊዶች በጋራ በመገንባት አብሮነታቸውን የማጠናከር ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስታውቋል። 

መላው ኅብረተሰብ በተለይም ወጣቱ ተግባሩን ከማውገዝ ባሻገር አንድነትን በማጠናከር በጉዳዩ ላይ መተባበር እንደሚገባም ጉባዔው ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም