ቀጥታ፡

የጽንስና ማህጸን ህክምና ጥራትን ለማስጠበቅ የሐኪሞች ማህበር የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጠል ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ጥር 28/2011 በኢትዮጵያ የሚሰጠውን የጽንስና ማህጸን ህክምና ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሙያው የተሰማሩ ሐኪሞች ማህበር የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። 

የኢትዮጵያ የጽንስና የማህጸን ሐኪሞች ማህበር ''ጥራትን፣ ፍትሃዊ ተደራሽነትንና ክብር የሚሰጥ የስነ ተዋልዶ አገልግሎት'' በሚል መሪ ቃል 27ኛ ዓመታዊ ጉባዔውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሄደ።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ህክምና ጥራትን ለማስጠበቅና ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ የሐኪሞች ማህበር አስተዋጽኦ ጉልህ ነው። 

ኢትዮጵያ የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ የያዘችውን ግብ ለማሳካት ሐኪሞች በጋራ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በተለይ ጥራትን መሰረት ያደረገና ስብዕናን የተላበሰ አገልግሎት ለእናቶችና ለህጻናት በመስጠት አገራዊ የጤና ግብን ለማሳካት የማህበሩ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ሚኒስቴሩ ከማህበሩ ጋር በመተባበር በጽንስና ማህጸን ህክምና ለሐኪሞች የሚሰጠው ስልጠና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆንና ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት በኩል ባለፉት ጊዜያት በርካታ ተግባራት መከናወኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ የጽንስና የማህጸን አገልግሎት ሰጪ ሐኪሞች ቁጥር ካለው የህዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጻር በጣም አነስተኛ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሊያ መንግስት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት በአሁኑ ወቅት ቁጥሩን ወደ 400 ከፍ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

ባለፉት ሁለት አስርታት የጽንስና ማህጸን ህክምና ይሰጥ የነበረው በአንድ የህክምና ተቋም ብቻ እንደነበረ አስታውሰው በአሁኑ ወቅት በአስር ተቋማት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የጽንስና የማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ባለይሁን በቀለ እንዳሉት፤ ማህበሩ በማህጸንና ጽንስ ህክምና ላይ ያሉ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች በኢትዮጵያ እንዲተዋወቁ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ የስነ ተዋልዶ መመሪያዎችና ደንቦች ሲዘጋጁ ማህበሩ ከሚኒስቴሩና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የጽንስና ማህጸን ህክምና አገልግሎትን በክልሎች ተደራሽ ለማድረግና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ማህበሩ ከክልሎች ጋር በትብብር የሚሰራውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ማህበሩ ግዴታውን እንደሚወጣም ዶክተር ባለይሁን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የጽንስና የማህጸን ሐኪሞች ማህበር የተመሰረተው እ.አ.አ በ1992 ሲሆን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የእናቶችንና የህጻናትን ጤና ለማስጠበቅ ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም