ቀጥታ፡

በኦሞና ማጎ ብሔራዊ ፓርኮች ህልውና ላይ የተደቀነው አደጋ አሳሳቢ መሆኑን ባለሥልጣኑ ገለጸ

አርባምንጭ ጥር 28/2011  በኦሞና ማጎ ብሔራዊ ፓርኮች ህልውና ላይ የተደቀነው አደጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለድርሻ አካላት የጋራ ምክክር መድረክ ዛሬ በጂንካ ከተማ መካሄድ ጀምሯል ፡፡

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን እንደገለጹት የኦሞና ማጎ ብሔራዊ ፓርኮች በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ህልውናቸው አደጋ ላይ ወድቋል ፡፡

የኢንቨስትመንት ልማት ፣ህገ ወጥ አደን፣ ግጦሽና ሰፈራ የችግሮቹ ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በችግሮቹ ምክንያት የዱር እንስሳት ዝርያዎች በመመናመንና በመ­ጥፋት ላይ እንደሚገኙ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።

አገሪቱ ከዘርፉ  ማግኘት ያለባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ ችግሮችን ለመፍታት ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

እስከ ጥር 30/2011 በሚቆየው የምክክር መድረክ  የፌዴራልና የደቡብ ክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የደቡብ ኦሞ ና የቤንች ማጂ ዞኖች አመራር አካላት ፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ሕዝብ ተወካዮች፣ የኪነ ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም