የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለመቄዶንያ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለመቄዶንያ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ፣ጥር 28/2011 የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል አምስት ሚሊዮን ብር በእርዳታ ሠጠ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ከጎበኙ በኋላ የተለያዩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ማዕከሉን በመጎብኘት ድጋፍ እያደረጉ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለማዕከሉ ባለ አምስት ፎቅ ህንጻ ለመገንባት ቃል መግባቱ ይታወሳል።
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ረሽድ ከማልም ከትናንት በስቲያ ማዕከሉን በመጎብኘት የአምስት ሚሊዮን ብር እርዳታ አድርገዋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ የቦርድ ውሳኔ መሠረት የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ለኢዜአ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ድጋፉ ማዕከሉ ለሚገነባው ሕንፃ ለመነሻነት እንዲውል ነው ብለዋል፡፡
አቶ ረሽድ በእርሳቸውና በቤተሰባቸውም ስም የ 10 ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውንም መቄዶንያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው ቤቶች መካከል ፒያሣ ወረዳ 2 የሚገኝ የንግድ ቤት በማዕከሉ የሚገኙ አረጋውያን ያመረቷቸውን ምርቶች ለመሸጥ በቋሚነት እንዲጠቀምባቸው ማበርከታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ ከሚያመርተው የጠጠር ምርት ለማዕከሉ ግንባታ ለማቅረብ ቃል መገባቱንም ነው የጠቀሱት፡፡
ከ 200 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ያገለገሉ ወንበሮችን፣ መደርደሪያዎችን፣ ምንጣፎችን፣ ቁምሳጥኖችን እና ጠረጴዛዎችን ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ገልፀዋል፡፡
ከውጭ አገራት ለሚመጡ በጎ ፈቃደኛ ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ፊዚዮቴራፒስቶች፣ መሃንዲሶች ዲዛይነሮች እና ለጎብኚዎች ማረፊያ ቤት ለመስጠት ቃል መገባቱንም አስታውቋል።
በተጨማሪም ማዕከሉ ለጀመረው ህንፃ ኮርፖሬሽኑ መሃንዲሶች፣ ባለሙያዎችን እና ግብዓቶችን ለመስጠትም ዋና ስራ አስፈጻሚው ቃል ገብተዋል፡፡
በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ማዕከሉ የጀመረውን የበጎ ተግባር ሥራ ለማስፋፋት የተለያዩ አካላት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።