ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለቡና ልማት ተስማሚ የሆነ መሬት አላት…የቡናና ሻይ ባለስልጣን

አዲስ አበባ ጥር 28/2011 በሀገሪቱ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሆነ መሬት ለቡና ልማት ከፍተኛ ተስማሚ እንደሆነ የኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለፀ።

ባለስልጣኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በኢትዮጵያ ለቡና ልማት ተስማሚ የሆነ ሰፊ መሬት አለ።

ለቡና ልማት በጣም ምቹ ተብሎ ከተለየው ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በተጨማሪ ከ17 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመካከለኛ ደረጃ ለቡና ልማት ተስማሚ ነው።

በአጠቃላይ 23 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከተሰራበት ከቡና ልማት ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል ባለስልጣኑ ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ በሚገኙ 184 ወረዳዎች ውስጥ ያሉ 4 ሺህ 64 ቀበሌዎች ከፍተኛ ቡና አብቃዮች መሆናቸው ተጠቁሟል።

በተጓዳኝ ቡና የሚያመርቱ 164 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 3 ሺህ 184 ቀበሌዎች እንዳሉ ባለስልጣኑ አመልክቷል።

ባለፉት ሶስት የበጀት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች በ1 ሚሊዮን 388 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአዲስ የቡና ተከላ ልማት መካሄዱን ገልጿል።

ያረጁ የቡና ተክሎች በአዳዲስ የቡና ተክሎች ባለመተካታቸው በምርታማነት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝም ጠቁሟል።

በአገሪቱ ካለው የቡና ሀብት ከ60 እስከ 70 በመቶ ያረጀ ቡና በመሆኑ ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ለዚህም አገራዊ የቡና ጉንደላ (ዕደሳ) ንቅናቄ እየተደረገ እንደሚገኝም ባለስልጣኑ በመግለጫው አብሯርቷል።

በተያዘው በጀት ዓመት በአገሪቱ ዋና ዋና ቡና አምራች ክልሎች 1 ሚሊዮን 129 ሺህ 620 ሄክታር መሬት ምርት መስጠት በሚችል የቡና ማሳ 786 ሺህ 766 ቶን ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚገመትም አመልክቷል፡፡

በአገሪቱ 2 ሚሊዮን 517 ሺህ 681 ሄክታር መሬት በቡና የተሸፈነ መሬት እንዳለና ከዚህ ውስጥ  1 ሚሊዮን 129 ሺህ 623 ሄክታር መሬት ምርት መስጠት የሚችል  ሲሆን 1 ሚሊዮን 388 ሺ ሄክታሩ ወደ ምርት ያልገባ አዲስ የቡና ተከላ የተካሄደበት መሬት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የተሻለ የማምረት ደረጃ ላይ በደረሱ አርሶ አደሮች ማሳ በሄክታር 15 ኩንታል የሚገኝ ሲሆን ሌሎች አርሶ አደሮች በሄክታር 6 ነጥብ 96 ኩንታል ምርት በማግኘት ላይ መሆናቸውን ባለስልጣኑ ለኢዜአ ካደረሰው መረጃ ለመገንዘብ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም