የሊጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ጥር 28/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ነገ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲዮም አዳማ ከተማ የፕሪሚየር ሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናግዳል።
በተመሳሳይ ሰዓት በትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ደደቢት ከመከላከያ ጨዋታቸውን የሚያካሂዱ ሲሆን ከቀኑ 11 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲዮም ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና ይጫወታሉ።
ከነገ በስቲያ ሦስት ጨዋታዎች በክልል ከተሞች የሚካሄዱ ሲሆን በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ባህርዳር ከተማ ከስሑል ሽረ፣ በትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲዮም መቀሌ 70 እንደርታ ከፋሲል ከተማ፣ በጅማ ስታዲዮም ጅማ አባ ጅፋር ከድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በተለያዩ ምክንያቶች ያልተካሄዱ ቀሪ ሰባት ተስተካካይ ጨዋታዎች እስከ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ እንደሚከናወኑ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ25 ነጥብ ሲመራ፣ መቀሌ 70 እንደርታና ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 23 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ሲይዙ ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
መከላከያ፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በዘጠኝ ግቦች ሲመራ፣ የሀዋሳ ከተማው ታፈሰ ሰለሞን፣ የመቀሌ 70 እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ የአዳማ ከተማው ዳዋ ሁቴሳና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ በስምንት ግቦች ይከተላሉ።