ቀጥታ፡

የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ ተራዘመ

አዲስ አበባ ጥር 28/2011 በ15ኛ ሳምንት ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ የቀን ለውጥ ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ቅዳሜ የካቲት 2 ቀን 2011 ዓ.ም በመቐለ ዓለም ዓቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሲዳማ ቡና ጋር ጨዋታቸውን እንዲያካሂዱ መርሃ ግብር ወጥቶላቸው ነበር። 

ፌዴሬሽኑ እንዳስታወቀው በተለያየ ምክንያት የውድድር መርሃ ግብሩን ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ወደ ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2011 ዓ.ም ተላልፏል።

ሌሎች የሳምንቱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በወጣው መርሃ ግብር መሠረት እንደሚካሄዱ ታውቋል።

በሌላ በኩል ጥር 19 ቀን 2011 ዓ.ም በድሬዳዋ ስታዲየም ሳይካሄድ የቀረው የድሬዳዋ ከተማ እና የሲዳማ ቡና የ13ኛ ሳምንት ጨዋታ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም ቀን 9፡00 ሰዓት ላይ እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የተራዘመው በድሬዳዋ በነበረው የፀጥታ ችግር ሲሆን ጨዋታው እንዲራዘም ክለቦቹ ባደረጉት ስምምነት መሆኑን ፌዴሬሽኑ ለኢዜአ መግለጹ የሚታወስ ነው። 

የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ፌዴሬሽኑ ያወጣው የውድድሩ መርሃ ግብር ቢያሳይም በተለያየ ምክንያት ያልተካሄዱ ጨዋታዎች በመኖራቸው በተስተካካይ መርሃ ግብር ውድድሩ እስከ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም