በካንሰር የሚደርሰውን ሰብአዊ ጉዳት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ፖሊሲ አውጪዎችን ማሳተፍ ያስፈልጋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በካንሰር የሚደርሰውን ሰብአዊ ጉዳት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ፖሊሲ አውጪዎችን ማሳተፍ ያስፈልጋል ተባለ
አዲስ አበባ ጥር 27/2011 በኢትዮጵያ በካንሰር ህመም ምክንያት የሚደርሰውን ሰብአዊ ጉዳት ለመከላከል ጠንካራ ማዕከል መመስረትና በመከላከል ተግባሩም ፖሊሲ አውጪዎችን ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ብዙም የማይታወቅ የነበረው የካንሰር ህመም በአሁኑ ወቅት በአሳሳቢ ደረጃ አየተስፋፋ መጥቷል ነው የተባለው።
የአለም የካንሰር ቀን " እራሴን፣ ቤተሰቤንና ወገኔን ከካንሰር ህመም ለመከላከል ቆርጬ ተነስቻለው!" በሚል መሪ ቃል ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተከብሯል።
በዚሁ ወቅት እንደተገለፀው የካንሰር ህመም የሰው ልጅን ህይወት የመቅጠፍ ደረጃው ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ፣ የሳባ ነቀርሳና የወባ ህመም ተደምረው ከሚያደርሱት ጉዳት ይበልጣል።
በኢትዮጵያ ብቻ በየዓመቱ ከ67 ሺህ በላይ ሰዎች በካንሰር ህመም የሚያዙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 44ሺህ ያህሎቹ በህክምና አገልግሎት እጥረት ሳቢያ ለሞት እንደሚዳረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የሰዎች ለሰዎች ግብረ-ሰናይ ድርጅት ፕሬዝዳንት ዶ/ር እናውጋው መሐሪ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የራሱ በጀት፣ ኮሚቴ እና የትብብር ማዕቀፍ መመስረት ብቻውን በቂ አይሆንም፤ የአገሪቱ መንግስት ቁርጠኛ ፖለቲካዊ ውሳኔም ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደሚሉት 52 በመቶ የሚሆነው የማህበረሰብ ክፍል ካንሰርን ጨምሮ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እየተጠቃ ነው፤ በዚህም ከፍተኛ ተጠቂዎቹ ሴቶች ናቸው።
በዚህም የተነሳ ችግሩ በአገሪቱ ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታዎች ላይ የከፋ አሉታዊ ተፅእኖ እያደረሰ ነው ብለዋል።
ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል የሚጠቀሰውን ካንሰር ለመከላከል ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑና እድሚያችው ከ9 እስከ 14 ዓመት ለሆኑ ልጃ ገረዶች የካንሰር መከላከያ ክትባት መሰጠቱን ገልፀዋል።
በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ያጋጠሙ ካሉት ችግሮች መካከል የመድሃኒት እጥረትና የህክምና አገልግሉት ተቋም በቂ አለመሆን ዋነኛዎቹ መሆናቸውንም ሚኒስትር ዲኤታዋ አክለዋል።
ብሄራዊ የካንሰር ኮሚቴ ሰብሳቢ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በኢትዮጵያ በተለይ የማህፀንና የጡት ካንሰር ህመምን ለመከላከል የህክምና ተቋማትን ማስፋፋት ይገባል ብለዋል።
መንግስት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት በአሁኑ ወቅት በጅማ፣ ጎንደርና መቐለ ከተሞች የካንሰር ህክምና የሚሰጡ ማእከላት እየተገነቡ መሆኑን አንስተዋል።
ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸውን እንዳያጡ ሁሉም የበኩሉን ሚና በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የካንሰር በሽታ ዋነኛ መንስኤዎች ሲጋራ፣ የአልኮል መጠጥ፣ በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ናቸው። በስነ ስርዓቱ ላይ እንደተገለፀው 41 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አልኮል ተጠቃሚ ናቸው።
ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካንና ናይጀሪያን ተከትላ በአፍሪካ 3ኛ ቢራ በብዛት የሚሸጥባት ሀገር እንደሆነችም ተጠቅሷል።
የዓለም ካንሰር ቀን በኢትዮጵያ ሲከበር ይህ ለ12ኛ ጊዜ ነው።
ቀኑ በበሽታው ምክንያት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመጠቆም፣ ለመከላከል ቅድመ ሁኔታዎችንና አገልግሎት አሰጣት ስርዓትን ለማበጀት እንዲሁም መደረግ ያለባቸውን መንግስታዊ ድጋፎች ለማመላከት ያለመ ነው።
ቀኑ የተከበረው የአለም ጤና ድርጅት፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ሰዎች ለሰዎች የተባለው ግብረ-ሰናይ ድርጅት እና ማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ በጋራ ትብብር ባዘጋጁት ሁነት ነው።