ቀጥታ፡

በጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተቋም የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ተባለ

አዲስ አበባ  ጥር 27/2011 የኢትዮጵያ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሰራተኞች የመልካም አስተዳደር ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ገለፁ።

ሰራተኞቹ በሥራ ቦታቸው እያጋጠማቸው ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር የገለጹት፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት፣ ውሃና መስኖ ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ በተቋሙ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ነው።

የተቋሙ የበላይ ኃላፊዎች የሚያደርጉት ቁጥጥርና ክትትል እጅግ የላላ በመሆኑ በተቋሙ ውስጥ በየእለቱ ምን ዓይነት ተግባር እየተከናወነ ስለመሆኑ እንደማይታወቅ ነው ሰራተኞቹ የገለፁት። 

በውይይቱ ላይ ቅሬታቸውን ካቀረቡት መካከል ወይዘሮ ሽብሬ ወለተሰንበት ተቋሙ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እንኳን የለውም፤ ሰራተኛው ለሚያቀርባቸው የተለያዩ የመብትና የሥራ ጉዳዮች ምላሽ የሚሰጠው አካል ማግኘት ተቸግሯል ብለዋል።  

"በዚህም የተነሳ አቅም ያላቸው ሰራተኞች በየጊዜው ተቋሙን ለቀው ይሄዳሉ፣  ቁጥጥርና ክትትል ባለመኖሩ የተነሳም በለቀቀ ሰራተኛ ስም ሳይቀር ደሞዝ የሚከፈልበት አጋጣሚም አለ" ሲሉም አክለዋል። 

በየጊዜው የሚቀርቡ ሪፖርቶች ስኬትን ሊያመላክቱ ይችላሉ፤ ነገር ግን ከሪፖርቱ በስተጀርባ ያለውን እውነታ መንግስት ቢመለከት ሲሉ ሃሳባቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

የተቋሙ ሹፌር መሆናቸውን የሚገልፁት አቶ ዋሲሁን ብርቁ በበኩላቸው በዚህ ዓመት ለመስክ ሥራ ወደ ሱዳን ጠረፍ አካባቢ በተጓዙበት ወቅት ከሌሎች ባልደረባዎቻቸው ጋር ባልታወቁ ሰዎች ታግተው 15 ቀን ሲቆዩ ተቋሙ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳላደረገላቸው ገልፀዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባልና  የመድረኩ ሰብሳቢ ወይዘሮ በላይነሽ ታደሰ በተቋሙ ሰራተኞች የተነሱትን ችግሮች እንዳለ በመውሰድ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ መፍትሄ እንዲበጅላቸው እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

በሌላ በኩል ቋሚ ኮሚቴው በጨረታ ይወገዱ የተባሉት 76  ተሽከርካሪዎ እንዲሁም ከተጀመረ ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረው የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክትን ተልክቷል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ገብረስላሴ በዚሁ ወቅት ተሽከርካሪዎቹ 30 ዓመት አገልግሎት የሰጡ በመሆናቸው በአሁን ወቅት አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውንና በጨረታ እስኪወገዱ ድረሰም በጊቢው እንዲቆሙ መደረጉን ነው የተናገሩት።

ይሁንና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የተቋሙ ሰራተኛ ተሽከርካሪዎቹ ለተጨማሪ አመታት አገልግሎት መስጠት የሚችሉ መሆኑን በስፍራው ለተገኙት የኮሚቴው አባላት ጠቁመዋል።

ለቢሮ አገልግሎት ተብሎ የተጀመረው የውሃ ጉድጓድ ሥራ እስካሁን ለምን እንዳልተጠናቀቀ በኮሚቴው ለቀረባለቸው ጥያቄም ዋና ዳይሬክተሩ ሲናገሩ በአሁኑ ወቅት የቀረው ሥራ የውሃ ፓምፕ መግጠም መሆኑን ጠቁመው ይህንን ተግባር ለመፈፀም ውል ከገቡት አካላት ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ ሥራው ሊጓተት መቻሉን አብራርተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የተቋሙ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መልካም የሚባል ቢሆንም ከሰራተኞቹ ጋር ባደረገው የውይይት መድረክና በመስክ ምልከታው ክፍተቶች ማስተዋሉን አስታውቋል።

በመሆኑም ተቋሙ ክፍተቶቹን ለመድፈን ብሎም በሰራተኞቹ የተነሱትን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ራሱን መፈተሽ እንዳለበት ቋሚ አሳስቧል።

ይህ መከናወኑ ለማረጋገጥም ተቋሙ ላይ ተከታታይ ክትትል እንደሚያደርግ ቋሚ ኮሚቴው በዚሁ ወቅት አስገነዝቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም