ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የካሜሮኑ ቱር ደ ዴሌስፖይር የብስክሌት ውድድር ተጀመረ

አዲስ አበባ ጥር 27/2011 ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 የአፍሪካ አገራት የሚሳተፉበት ሁለተኛው የካሜሮን ቱር ደ ዴሌስፖይር የብስክሌት ውድድር ዛሬ ተጀምሯል።

የዓለም አቀፉ የብስክሌት ህብረት(ዩሲአይ) እና የፈረንሳዩ የስፖርት ውድድሮች አዘጋጅ ተቋም ቪቬንዲ ስፖርት በጋራ ያዘጋጁት ውድድር እድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች የሆኑ ብስክሌተኞች ይሳተፉበታል።

በውድድሩ ላይ ከአፍሪካ አገራት በተጨማሪ የአርጀንቲና፣ኢኳዶር፣ፖርቹጋል፣ጃፓንና የጀርመን ብስክሌት ቡድኖች የሚሳተፉ ይሆናል።

ወንድ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች በሚሳተፉብት በዚሁ ውድድር ኢትዮጵያ በነጋሲ ሃይሉ፣በሬድዋን ሳሊህ፣ሚሊዮን ቤዛ፣ታምራት መረሳ፣ክብሮም ተክለብርሃንና በክብረአብ ተክለ ሃይማኖት ትወከላለች።

የካሜሮኑ ቱር ደ ዴሌስፖይር የብስክሌት ውድድር የኢትዮጵያ የብስክሌት ቡድን ንጉሴ ገብረዮሐንስ በአሰልጣኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፍጹም ወልደአብ ለኢዜአ እንደገለጹት የውድድሩ አላማ በአፍሪካ ብቃት ያላቸውን ብስክሌተኞች ለማፍራት ነው።

የኢትዮጵያ የብስክሌት ቡድን በየክለባቸው ለውድድሩ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተው ከትናንት በስቲያ ወደ ውድድሩ ስፍራ ማቅናታቸውንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት በፊት በጋቦን በተካሄደው የቱር ጋቦን የብስክሌት ውድድር ላይ ተሳትፋ ሶስተኛ መውጣቷንም አቶ ፍጹም ገልፀዋል።

በአምስት የካሜሮን ከተሞች የሚካሄደው የቱር ደ ዴሌስፖይር የብስክሌት ውድድር በአምስት ዙር 403 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር በመሸፈን ተካሄዶ የካቲት 2 ቀን 2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

የቱር ደ ዴሌስፖይር የብስክሌት ውድድር በዓለም አቀፉ የብስክሌት ህብረት(ዩሲአይ) የ2 ነጥብ 2 ደረጃ በሚለው የውድድር አይነት (ካታጎሪ) የሚካተት ነው።

በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ ብስክሌተኞች በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ በሚካሄደው የቱር ደ አቬኒር የብስክሌት ውድድርና በታላቋ ብሪታኒያ በመስከረም 2012 ዓ.ም በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር የሚሳተፉ ይሆናል።

በካሜሮን በተካሄደው የመጀመሪያው የብስክሌት ውድድር ኢትዮጵያ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ ሩዋንዳ አንደኛ እንዲሁም ሞሮኮ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም