በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የቂርቆስና ኮልፌ ቀራኒዮ ክለቦች ድል ቀንቷቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የቂርቆስና ኮልፌ ቀራኒዮ ክለቦች ድል ቀንቷቸዋል
አዲስ አበባ ጥር 27/2011 በዘንድሮው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች በሊጉ አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።
የፕሪሚየር ሊጉ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንትና ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች ተካሄደዋል።
በዚሁ መሰረት ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መከላከያን 36 ለ 30 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በሊጉ አራተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ትናንት በተደረገ ሌላ ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቡታጅራ ከተማን 42 ለ 25 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
ውጤቱንም ተከትሎ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ አራተኛ ድሉን ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን ከአምናው የሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጠንካራ ፉክክር በማድረግ ላይ ይገኛል።
በአንጻሩ ቡታጅራ ከተማ እስካሁን በሊጉ ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች ተሸንፏል።
በክልል ከተሞች ትናንት ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል።
ጎንደር ላይ ፌደራል ፖሊስ አዲሱ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሆነውን ጎንደር ከተማ 18 ለ 16 አሸንፏል። ጎንደር ከተማ እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም።
መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ያደረጉት ጨዋታ 25 ለ 25 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ድሬዳዋ ከተማን 34 ለ 11 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት አንድ ቡድን ሲያሸንፍ ሁለት ነጥብ አቻ ሲወጣ አንድ ነጥብ ያገኛል።
በዚሁ መሰረት የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ ስምንት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን መቐለ ሰብዓ እንደርታ በሰባት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቡታጅራ ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።
በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 10 የእጅ ኳስ ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።