ቀጥታ፡

የኖርዌይ ዓለም ዓቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር ኢትዮጵያ መጎብኘት ጀመሩ

ጥር አዲስ አበባ 27/5/2011 በኢትዮጵያ  ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኖርዌይ ዓለምዓቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር ዳግ ኢንግ ኡልስታይን አስታወቁ።

የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልበርግ በሚቀጥለው ሳምንት በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሚኒስትሩ ለአራት ቀናት በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉብኝት ዛሬ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በመወያየት   ጀምረዋል።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ በቅርብ እየተከታተሉ መሆኑንና ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ጋር ባካሄዱት ውይይት ድጋፋቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።

ኢትዮጵያና ኖርዌይ ዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን የጀመሩት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ሲሆን በትምህርት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በስደተኞች ጉዳይ ላይ በትብብር ይሰራሉ።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው እንደገለጹት፤ የኖርዌይ ዓለምዓቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር ዳግ ኢንግ ኡልስታይን በኢትዮጵያ የአራት ቀናት ቆይታ ይኖራቸዋል።

በዚህም ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ጋር እንደሚወያዩና በኖርዌይ የልማት ትብብር ድጋፍ የተሰሩ የልማት ስራዎችን እንደሚጎበኙ ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ የኖርዌይ ዓለምዓቀፍ ልማት ትብብር ሆነው የተሾሙት ባለፈው ሳምንት ሲሆን በመጀመሪያ ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ በመጀመራቸው በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የልማት አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት።

ኖርዌይ 12 የልማት አጋሮች ብላ ከለየቻቸው አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም እ.ኤ.አ በ2017 የመጀመሪያውን የቀጥታ በረራ ወደ ኖርዌይ በማድረግ ከአፍሪካ አየር መንገዶች የቀዳሚነቱን ስፍራ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም