በመኖሪያ ቤቶች አቅራቢያ የሚገነቡ ፋብሪካዎች የሚያደርሱትን አደጋ ለመከላከል ተቋማት የተቀናጀ መፍትሄ ይስጡ..ነዋሪዎች

ጥር 26 /2011 በመኖሪያ አካባቢዎች የሚገነቡ ፋብሪካዎች በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሱትን አደጋ ለመከላከል ተቋማት ተቀናጅተው በመስራት መፍትሄ እንዲሰጠው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት በተለያዩ አካባቢዎች በመኖሪያ ስፍራዎች እየተገነቡ ያሉ ፋብሪካዎች በህብረተሰቡ ላይ የሚያስከትሉትን የተለያየ አደጋዎች ለመከላከል የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አበበ ታሪኩ በሚኖሩበት ሳንሱሲ አካባቢ በመኖሪያ ጊቢ ውስጥ ሳይቀር የሻማ ፤ የጁስ፣ የቅባት የፕላስቲክ የፕላስቲክ ጫማ ፋብሪካዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከእነዚህ ፋብሪካዎች በሚለቀቅ ፍሳሽና ጭስ ህብረተሰቡ ለጤና ችግር የሚጋለጥበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

በቡራዩ ሸክላ አካባቢ ነዋሪ አቶ አለሙ ጎበና በበኩላቸው በቅርቡ በአካባቢያቸው በነበረ  የሻማ ፋብሪካ ቃጠሎ በአካባቢው በነበሩ የመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን በማንሳት  በአካባቢያቸው የእንጨት መሰንጠቂያና ማዳበሪያ ፋብሪካ ሳይቀር በመንደር ውስጥ እንደሚገኝ  ጠቅሰዋል፡፡

በቃጠሎው ጉዳት ከደረሰባቸው ቤቶች በተጨማሪ በአደጋው ሳቢያ ከፋብሪካው የወጣው መርዛማ ፍሳሽ በጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል መሆኑ በመነገሩ አስር ሺህ ብር በመክፈል እንዲወገድ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በከተማው የኮተቤ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ አበበች ዳምጤ በሰጡት አስተያየት በከተማዋ  በመኖሪያ ስፍራዎች የሚገነቡ ፋብሪካዎች ግንባታቸው በፕላን ባለመሆኑ በነዋሪው ላይ ችግር ሲፈጥሩ ይስተዋላል ብለዋል፡፡

በነዋሪዎች መንደር ከፍተኛ ድምፅ የሚያወጡ የእንጨት መሰንጠቂያና የቤት እቃ መስሪያ መለስተኛ ፋብሪካዎች በየቦታው እየተበራከቱ እንደሚታዩ አንስተው፤ ወይዘሮ አበበች ለእነዚህ ፋብሪካዎች ፍቃድ የሚሰጠው አካል ሌሎች ከሚመለከታቸው  ሴክተሮች ጋር  በእቅንጂት መስራት እንደሚገባ  ጠቅሰዋል

ሌላው የከተማው ነዋሪ  ወጣት ሸምሱ ታደሰ በበኩላቸው በአብነት ፓስተር አደባባይና ዊንጌት አደባባይ ላይ የሚወጣው የቆዳ ፋብሪካ ፍሳሽ ጠረን  ለአካባቢው ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን በመንገዱ ለሚጠቀሙ ሰዎች ጭምር ችግር ሲፈጥር የሚስተዋል በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ብሏል፡፡

በመኖሪያ ቤቶች አቅራቢያ የፋብሪካዎች መበራከት ጋር የተነሳው ጥያቄ መሰረታዊ ነው  ለአብነት በቡራዩ በሻማ ፋብሪካ ላይ የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ  የመኖሪያ አካባቢ  መሆኑን የተናገሩት በአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለስልጣን የህዝብ ግኑኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ተሾመ ናቸው፡፡

በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ፋብሪካዎች እየተቋቋሙ እንደሚገኙና በአደጋ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከፋብሪካዎቹ በሚወጡ ፍሳሽና ጭስ ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ይታያል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በአካባቢያዊ የህብረተሰብ ጤና ምርምር ቡድን ተባባሪ ተመራማሪ አቶ አቤል ወልደተንሳይ እንደገለጹት ከፋብሪካዎች የሚለቀቁ ፍሳሽ፣ ሽታና ጭስ በህብረተሰቡ ላይ  የጤና ችግሮች ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ለአብነት ከቆዳ ኢንዱስትሪዎች በወጡ ፍሳሾች ላይ ባደረጉት ምርምር ከቆዳ በሸታና የመተንፈሳሻ አካላት ጉዳት እስከ ካንሰር ሊደርሱ የሚችሉ በሽታዎች በህብረተሰብ ላይ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በምርምራቸው ማረጋገጣቸውን ነው ያብራሩት፡፡

ጉዳቱ ወቅታዊ በሽታ በማስከተል ብቻ የሚቆም አይደለም የሚሉት ተመራማሪው  ወደትውልድ የመተላለፍ ተጽእኖ ያላቸው በሽታዎች የመፍጠር ሀይል እንዳላቸውም ነው የተናገሩት፡፡

ተመራማሪው እንዳሉት ፋብሪካዎች መገንባት ያለባቸው በአዲሱ አሰራር በኢንዱስትሪ ዞንና ለዘርፉ በተከለሉ አካባቢዎች  መሆን እንዳለባቸውና ዘርፉ በአግባቡና በስርዓት ከተመራ ከተረፈ ምርቱ ጉዳት ሳይሆን ጥቅም ሊገኝ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

በደን አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ የማህበረሰብ ተጽእኖ ግምገማ ዳይሬክተር  አቶ ቶሎሳ ያደሳ በበኩላቸው የህብረተሰቡ ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ተናግረው፤ ማንኛውም ፋብሪካ ወደ ግንባታ ፈቃድ ከመግባቱ በፊት ከኮሚሽኑ የይሁንታ ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህን የሚፈቅዱ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ አስተዳደሮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተውና ተናበው ባለመስራታቸው ችግሩ እስካሁን መቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኮሚሽኑ በተለይ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር የተቀናጀ አሰራር በመፍጠሩ በህብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ለሚችሉ ፋብሪካዎች ፍቃድ የማይሰጥበት ሁኔታ ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ የወጣውን የአካባቢ ጥበቃ አዋጅአቶ ቶሎሳ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም