የቀድሞ አፈ-ጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞ አፈ-ጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈጸመ
አዲስ አበባ ጥር 26/2011 የቀድሞ አፈ-ጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ የቀብር ስነ-ስርዓት ዛሬ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።
በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የቀድሞና የአሁን የፌዴራል መንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የክልሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
የቀድሞ አፈ-ጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ ክብር ሲባል መለስተኛ መሳሪያ ተተኩሷል።
የቀድሞው አፈ-ጉባዔ ዳዊት ዮሃንስ ለዘመናዊ ፓርላማ አሰራርና የዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።
አቶ ዳዊት የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም መጽደቁን ተከትሎ የመጀመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ በመሆን እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል።
አቶ ዳዊት በአፈ-ጉባዔነት የስራ ዘመናቸው ለዘመናዊ ፓርላማ አሰራርና የዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር የነበራቸው አበርክቶ ከፍተኛ ነበረ።
በምክር ቤት አፈ-ጉባዔነታቸው የመጀመሪያው እንደ መሆናቸው ዛሬ ላይ ላለው ዘመናዊ የፓርላማ አሰራር ከፍተኛ አስተዋኦ ያበረከቱ ናቸው።
በምክር ቤቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጠናከር፣ መርቀቅ ያለባቸው ህጎች እንዲረቀቁ፣ አስፈጻሚውን አካል በአግባቡ እንዲከታተልና የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀት የራሱን ስራ በነጻነት እንዲሰራ ለማስቻል ጥረት አድርገዋል።
አቶ ዳዊት ከስራ ታታሪነታቸው ባሻገር በግል ህይወታቸውም ሁሉን በእኩል ዓይን የሚያዩ፣ ሩህሩህና ለተቸገረ ደራሽ እንደነበሩ በስራ ዘመናቸው አብረዋቸው የሰሩ ሁሉ ይናገራሉ።
አቶ ዳዊት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 21 ቀን 2011 ዓ.ም መግለጹ ይታወሳል።
የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በአሜሪካው ጆርጅ ታውንና በኔዘርላንዱ አምስተርዳም ዩኒቨርሲቲዎች ተከታትለዋል።
የጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳዊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም በሰሩበት ጊዜ በደቡብ ሱዳን የሠላም ግንባታ፣ በቻይናና አፍሪካ ግንኙነት፣ በሠላም ማስከበርና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ጥናቶች አካሂደዋል።
አቶ ዳዊት ዮሃንስ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ።