ቀጥታ፡

በመንግስት በኩል በርካታ ግድቦችን የመስራት ፍላጎት አለ - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባ ጥር 26/2011 በመንግስት በኩል በርካታ ግድቦችን የመስራት ፍላጎት እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

ከአዲስ አበባ በ365 ኪሎ ሜትር ርቀት፣ ከዲላ ከተማ አቅራቢያ ጊዳቦ በተሰኘ የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ቦታ ላይ የተገነባው የጊዳቦ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት ዛሬ በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውና የአገር ውስጥ እውቀትና ጉልበትን አስተባብሮ የተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ ለአሳ እርባታ፣ ለከባቢ አየር ጥበቃ፣ ለአረንጓዴ ልማት፣ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራና እንዲሁም የግብርና ምርትን በማሳደግ በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። 

የግድቡ ግንባታ መቶ በመቶ በኢትዮጵያውያኖች መሰራቱ በሌሎች ሀይሎች የሚሰራና በብድር የሚሰራ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ትኩረት በመስጠት ያለውን የአገር በቀል አቅምን የመጠቀም ችግር እንደሚቀርፍ አመልክተዋል።

''ሰው ያለውን ነገር ሳያለማ የሌለውን መሻት የለበትም'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሃ፣ መሬት፣ ጉልበትና ጭንቅላት አስተባብሮ ቢጠቀም አካባቢን መቀየር እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

ውሃ መሬት ጉልበት ብቻ ሳይሆን ያንን አስተሳስሮ ማልማት የሚችል ጭንቅላት በኢትዮጵያ መፈጠሩ ትልቅ ጸጋ ሳያልፍብን መጠቀም እንደሚገባም አመልክተዋል።

የጊዳቦ ግድብ ወንድማማች የሆነውን የሲዳማና ጉጂ ህዝብ የሚያቀራርብ አብሮ መስራት፣ መልማት፣ ማደግና መኖር እንደሚቻል የሚያሳይ እንደሆነም ገልጸዋል።

ወደፊትም የፌዴራል መንግስት በየክልሎች ያሉትን ህዝቦች የሚያስተሳስር የጋራ ፕሮጀክቶችን እየቀረጸ ህዝቦች በጋራ እንዲሰሩ በጋራ እንዲያለሙና በጋራ እንዲለሙ የሚጠበቅበትን ስራ በተለየ ትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የጊዳቦ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት በተባለለት ጊዜ ያልተጠናቀቀና ከፍተኛ ወጪ ያስወጣ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በቀጣይም መንግስት በርካታ ግድቦችን የመገንባት ፍላጎት እንዳለውና ይህም መሆኑ ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት ኢኮኖሚያዊ አቅሟን ለማሳደግ እንደሚያስችላት አስረድተዋል።

"ስንዴ እየለመንን ድንጋይ የምንወረውር ሳይሆን ስንዴ እያለማንና እየበላን ሀሳብ የምንወረውር ትውልዶች እንድንሆን ግድብ ያስፈልገናል" ብለዋል።

መንግስት በቀጣይ ዋንኛ ትኩረቱ መስኖ ልማትና ግብርና በመሆኑ በዘርፎቹ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ ዛሬ ተመርቆ የተከፈተው ግድብ ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚያዊና የልማት ተጠቃሚነት እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

በክልሎቹ እየተገነቡ ያሉ ሌሎች የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የክልሎቹን ህዝቦች ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የጊዳቦ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት የተጓተተው በተቋራጮችና አማካሪዎች የአቅም ውስንነትና በዲዛይን መቀየያየር እንደሆነ ገልጸዋል።

ግድቡ ከጅማሮው ጊዜ አንስቶ በርካታ ፈተናዎችና ውስብስብ ችግሮች ገጥመውት እንደነበርም አስታውሰዋል።

አሁን በግንባታ ላይ የሚገኙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ርብርብ እንደሚደረግና የሚመለከታቸው አካላትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የርብ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ከስድስት ዓመት መጓተት በኋላ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ.ም መመረቁ ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ከአስር ዓመታትና ከዚያም በላይ የተጓተቱ የግድብና የመስኖ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ።

የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶች፣ የተንዳሆና የከሰም ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ከተጓተቱት ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የግድቦቹ ግንባታ መጓተት በአገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ብክነት በማስከተል በኢኮኖሚው ላይ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሆነና ጉዳዩ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኝ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም