ቀጥታ፡

ሁለተኛው ብሔራዊ የክለቦች ቦክስ ውድድር በወላይታ ሶዶ ከተማ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ጥር 26/2011 ሁለተኛው ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር በወላይታ ሶዶ ከተማ ከጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ይካሄዳል።

በሁለቱም ጾታዎች በሚካሄደው ውድድር ከ10 ክለቦች የተወጣጡ 70 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሏል።

የመጀመሪያው ዙር ውድድር አሸናፊ የድሬዳዋ ከተማ የቦክስ ክለብ ፣ማራቶን፣ወላይታ ጦና፣አዲስ አበባ ፖሊስ፣ፌደራል ፖሊስና ፌደራል ማረሚያ ቤቶች በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ።

በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ውድድር የሚካሄድ ይሆናል።

የውድድሩ አላማ በስፖርቱ ብቁና ውጤታማ ተወዳዳሪዎችን መመልመልና የውድድር አማራጭ መፍጠር እንደሆነ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሞሮኮ አዘጋጅነት ከነሐሴ 17 እስከ 28 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በቦክስ ስፖርት ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ እንደሚረዳም ተናግረዋል።

ብሔራዊ የክለቦች ቦክስ ውድድር በዓመት አራት ጊዜ እንደሚካሄድና የመጀመሪያው ውድድር ህዳር 2011 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ እንደተካሄደ ያስታወሱት አቶ ስንታየሁ፤ ቀጣዮቹ ሁለት ውድድሮች በጅግጅጋና አዲስ አበባ እንደሚካሄዱም አመልክተዋል።

በቦክስ ውድድሮቹ የተገኘው አጠቃላይ ውጤት ተሰልቶ በሁለቱም ጾታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦች የ2011 ዓ.ም የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚሆንም አስረድተዋል።

በህዳር 2011 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው የዓመቱ የመጀመሪያ ብሔራዊ የክለቦች ውድድር የድሬዳዋ ከተማ የቦክስ ክለብ በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም