የመንግሰት ግዙፍ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዛወሩ ስራ በጥንቃቄ ሊከናወን ይገባል- የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሰት ግዙፍ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዛወሩ ስራ በጥንቃቄ ሊከናወን ይገባል- የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁራን
መቀሌ ጥር 26/2011 የመንግሰት ግዙፍ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዛወሩ ስራ በቅደም ተከተል፣ በቅንጅትና በጥንቃቄ ሊከናወን እንደሚገባ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ አንዳንድ ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ ለኢትዮዽያ ዜና አገልግልት እንደገለጹት ድርጅቶቹን ወደ ግል ይዞታ የማዛወሩ ስራ የፋይናስ ችግርን ከመፍታትና ብክነትን ከመቆጣጠር እይታ ብቻ መታየት የለበትም።
ዝውውሩ ዓለም አቀፍ የመደራደር አቅምን የሚጠይቅ፣የትኛው የልማት ፕሮጀክት ይዛወር የትኛውስ ይቆይ የሚል ቅደም ተከተልን የሚፈትሽና በመፈጸሙም የሚገኙ ትርፎችን በማጥናትና በመተንተን የሚከናወን ተግባር መሆኑን ምሁራኑ ገልጸዋል።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ኪዳነማርያም ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት ግዙፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወሩ ከፋይናንስ አቅምም በላይ ዓለም አቀፍ እውቀትን፣የቴክኖሎጂና የቴክኒክ ብቃትን ይጠይቃል።
የዝውውር ስራው በተረጋጋ ሁኔታ ሂደቱን ጠብቆ መፈጸም ያለበት መሆኑን የተቆሙት ዶክተር ኪዳነ ማርያም "ዝውውሩ አለም አቀፍ የመደራደር ብቃትንና የካፒታል ግብይት ስርዓትን ግምት ውስጥ ማስገባት የሚጠይቅ ነው" ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ በአብነት የጠቀሱት ምሁሩ ለዝውውሩ የሚያግዝ አቅም ባልተገነባበት ሁኔታ የመንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዛወሩ ስራ ከትርፍ ይልቅ ኪሳራን ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አመልክተዋል።
ተቋማቱን የሚረከበው ባለሀብት በቴክኖሎጂ ከማዘመን ጀምሮ በምርት ጥራት፣ በምርታማነትና እና በዋጋም ጭምር ከዚህ አንስቼ እዚህ አደርሰዋለሁ የሚል ስምምነት እና አስገዳጅ ድርድር መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል።
በዓለም አቀፍ የገንዘብ እርዳታ ድርጅቶችና የገንዘብ ተቋም ግፊት እንዲሁም በጥድፊያ ግዙፍ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶችን ወደ ግሉ የማዛወር ስራ መከናወን እንደሌለበትም አብራርተዋል።
በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የዲቨልመንታል ጥናት ትምህርት ክፍል ባልደረባና የማናጅመንት ምሁር ዶክተር ቢሆን ካሳ በበኩላቸው ድርጅቶቹን ወደ ግል ይዞታ ማዛወሩ የትኞቹን ተቋማት መቼ የሚለውን ጥያቄ በሚመልስ ዝርዝር ማስፈጸሚያ ሊከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጰያ አየር መንገድ፣ባንኮችና መሰል ተቋማትን ጨምሮ በትርፋማነታቸው በምርታማነታቸው የሚታወቁትን የልማት ፕሮጀክቶች በመንግስት ስር ማቆየት እንደሚገባም አስተያየቸውን ተናግረዋል።
"ባለሀብት በትርፍ ብቻ ነው የሚያምነው" ያሉት ዶክተር ቢሆን " በእንደኛ ያሉ አገራት የመንግስትን ጣልቃ ገብነት እጅግ ያስፈልጋል" ብለዋል።
የመንግስትን በጀት የሚበሉና ተከታታይ ኪሰራ ያለባቸው ፕሮጀክቶችን በመለየት ወደ ግል የማዛወር ስራ መሰራት እንዳለበት የጠቆሙት ምሁሩ ትርፋማ የሆኑ ተቋማትን በመለየት በመንግስት እጅ ማቆየት እንደሚገባ መክረዋል።
"በእኛ ሀገር የመንግስት ጣልቃ-ገብነት እጅግ ያስፈልጋል" ያሉት ዶክተር ቢሆን በሂደት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች አቅም እየተጠናከረ ሲሄድ ተቋማቱን የማዛወር ስራ ቢሰራ የተሻለ እንደሆነ አመልክተዋል።
ዝውውሩ በሚፈጸምበት ጊዜም ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል።
ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባም ምሁሩ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ልማትን አስመልክቶ በምሁራን የቀረበ መረጃ እንደሚያትተው ኢትዮጵያ በ1984 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገችው አዲስ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ከእዝ ወደ ነጻ ገበያ እንዳስገባትና ውጤትም እንደተመዘገበበት ተናግረዋል።
የዓለም ባንክ ሪፖርት እንዳመለከተውም በተጠናቀቀው 2018 የፈረንጆች ዘመን አቆጣጠር ላይ ኢትዮጰያ የ9 ነጥብ 6 በመቶ እድገት አስጠብቃ መሄዷን ገልጿል።