ቀጥታ፡

ሠራዊቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማስጠበቅና ሕዝባዊነቱን በማጠናከር ለአስተማማኝ ሰላም ይሰራል-ምዕራብ ዕዝ

ጋምቤላ ጥር 25/2011 መከላከያ ሠራዊት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማስጠበቅና የሕዝብ ወገንተኝነቱን በማጠናከር አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር ጥረት  እንደሚያደርግ የምዕራብ ዕዝ 12ኛ ክፍለ ጦር አስታወቀ፡፡

ክፍለ ጦሩ ለሰባተኛ ጊዜ የሚከበረውን የመከላከያ ሠራዊት ቀን አስመልክቶ ከጋምቤላ ክልል አመራሮችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዛሬ የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡

የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ብርጋዲዬር ጀኔራል አበበ በየነ እንዳሉት ሠራዊቱ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማስጠበቅና ሕዝባዊነቱን በማስቀጠል አገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ እውን ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡

ሠራዊቱ ሕዝባዊነትን በመላበስ የውስጥም ሆነ የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመመከት ግዳጁን በብቃት እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ክፍለ ጦሩ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት እንደሚወጣ ያረጋገጡት ዋና አዛዡ፣ ኅብረተሰቡ ለሰላም ዘብ በመቆም የሠራዊቱን ኃላፊነት ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው ሠራዊቱ ለህዝቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሲባል  ህይወቱን ጭምር በመስጠት  እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት የክልሉ መንግሥት አድናቆትና ከበሬታ እንዳለው ተናግረዋል።

ሠራዊቱ  በአገሪቱ ሰላም በማስፈን አስተማማኝ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካትም እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ሠራዊቱ እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም እንደሚደግፍና ከክልሉ ሕዝብ ጋር የነበረውን አብሮነት ለማጠናከር ፍላጎቱ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የተሳተፉ የአመራር አካላትና የኅብረተሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት ሠራዊቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችን ሰላም በማስጠበቅ ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን መስክረዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በልማቱ ዘርፍ በሚያደርገው ተሳትፎ በተለይም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በገንዘብና በጉልበት በማገዝ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አድንቀዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኡቶው ኮት በሰጡት አስተያየት ሠራዊቱ የአገሪቱን አንድነት በማስጠበቅ በኩል እየተወጣ ያለው ግዳጅ እንደሚያስመሰግነው አመልክተው፣ለዚህም በጋምቤላ ክልል ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታትና ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የነበረውን አስተዋጽኦ በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ በበኩላቸው ሠራዊቱ የአገሪቱን ሰላም ከማስከበር ውጭ በተለያዩ አገሮች ሰላም ለማስፈን እያከናወነ ያለው ተልዕኮ አድንቀዋል፡፡

በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዲኖር በደቡብ ሱዳንና  በሶማሊያ እያስመዘገበ ያለው ውጤት አመርቂ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የመከላከያ ሠራዊት አደረጃጀትን የሚያትት ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

''ሕገ-መንግሥታዊ ታማኝነታችንና ሕዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን አገራዊ ለውጡን እናስቀጥላለን! ''በሚል መሪ ቃል በመጪው የካቲት ሰባት የመከላከያ ሠራዊት ቀን ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም