መቀሌ 70እንደርታ መከላከያን ሲያሸንፍ ፤ጅማ አባ ጅፋርና ባህር ዳር ከተማ ነጥብ ተጋሩ - ኢዜአ አማርኛ
መቀሌ 70እንደርታ መከላከያን ሲያሸንፍ ፤ጅማ አባ ጅፋርና ባህር ዳር ከተማ ነጥብ ተጋሩ
ጅማ/መቀሌ ጥር 25/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ዛሬ በተካሄዱ ጨዋታዎች መቀሌ 70እንደርታ መከላከያን ሲያሸንፍ፣ጅማ አባጅፋር ከባህር ዳር ከተማ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።
መቀሌ ላይ በተካሄደው ጨዋታ መቀሌ 70እንደርታ መከላከያን አምስት ለሁለት በሆነ ውጤት አሸንፏል።
አማኑኤል ገብረ ሚካኤል በ29ኛው፣በ37ኛውና በ50ኛውና በ54ኛው ደቂቃዎች ለመቀሌ 70 እንደርታ አራት ግቦችን አስቆጥሯል።
ቀሪዋን አንድ ግብ ደግሞ ያሬድ ከበደ አስገብቷል።
አማኑኤል የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን በኮከብ ግብ አስቆጣሪነትም እየመራ ነው።
መከላከያ ምናለ ወንድሙ በ27ኛው ደቂቃ በጨዋታና በ88ኛው ደቂቃ ፁም ቅጣት ምት ሁለት ግቦች አስቆጥሯል።
መቀሌ 70 እንደርታ ክለብ ነጥቡን ወደ 23 ከፍ ያደረገ ሲሆን፣መከላከያ በ14 ጨዋታ10 ነጥብ ብቻ በማስመዝገብ ወራጅ ቀጣና ላይ ይገኛል።
የመቀሌ 70 እንደርታ አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ በሰጡት አሰተያየት ''ባቀድነው መሠረት አጥቅተን በመጫወታችን የምንፈልገው ውጤት አግኝተናል። ደስ ብሎኛል'' ብለዋል።
የመከላከያ ቡድን አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በሰጡት አስተያየት ''በጨዋታው ተበልጠናል ክፍተቶችን ተጠቅመው አሸንፈውናል። በቀጣይ ካለንበት ደረጀ ከፍ በማለት የነበረንን ክፍተቶች አስተካክለን ጥሩ ተፎካካሪ እንሆናለን'' ብለዋል።
ጅማ ላይ በተደረገው ጨዋታ ደግሞ ጅማ አባጅፋር ባህር ዳር ከተማ አንድ አንድ ለአንድ ተለያይተዋል።
ባለሜዳዎቹ ጅማ አባጅፋሮች በ45 ደቂቃ በማማዱ ሲዴቤ መሪ የሆኑባትን ግብ ያስቆጠሩ ቢሆንም፤ በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናክረው የገባው ባህር ዳር ከተማ በ58ኛው ደቂቃ ላይ በግርማ ዴሲሳ አማካኝነት አቻ ያደረገቻቸውን ግብ አስቆጥሯል፡፡
ጅማ አባጅፋሮች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም፤ በባህር ዳር በረኛ ጥረት ተጨማሪ ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ባህር ዳር ከተማ ኳስን ተቆጣጥሮ የተጫወተ ሲሆን፣ ጅማ አባጅፋሮች ረጅም ኳስ ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ሲጫወቱ ተስተውለዋል፡፡
ሶስት ያለቀላቸው ኳሶችን ሞክረው በባህርዳር በረኛ ብቃት መክኖባቸዋል፡፡
የጅማ አባጅፋሩ ኮክብ ግብ ጠባቂ ዳንኤል ኦጄ ተከቶ ዘሪሁን ታደለ ተጫውቷል።
በሌሎች ጨዋታ ሲዳማ ቡና ደደቢትን 3 ለ 0 ሲያሸንፍ ፣ አዳማ ከተማ ከወላይታ ድቻ 1ለ1 ተለያይተዋል
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ደግሞ ደቡብ ፖሊስ ኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ዘሪሁን አንሼቦ እና ዮናስ በርታ ለደቡብ ፖሊስ፤ አቡበከር ናስር ደግሞ ለኢትዮጵያ ቡና ግቦችን አስቆጥረዋል።
ፕሪሚየር ሊጉ ነገም ሲቀጥል ሐዋሳ ላይ ሐዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ፤ አዲስ አበባ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ይጫወታሉ።