በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የ200 ሴት ህጻናት ጋብቻ ተሰረዘ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የ200 ሴት ህጻናት ጋብቻ ተሰረዘ
ሽሬ እንዳሥላሴ ጥር 25/2011 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት የ200 ሴት ህጻናት ጋብቻ መሰረዙን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
ጋብቻው የተሰረዘው የክልሉን የቤተሰብ ህግ መሠረት በማድረግ ከህጻናቱ ወላጆቻቸውና አሳዳጊዎች ጋር በተደረሰ ስምምነት መሆኑን አስተዳደሩ ገልጿል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ አቶ እልፍዮስ ታደሰ ለኢዜአ እንዳስረዱ ጋብቻቸው የተሰረዘው ህጻናት በዞኑ ስድስት ወረዳዎች ሊዳሩ ዝግጅት የተደረገላቸው ናቸው።
ወላጆች ለሠርግ ሥነ ሥርዓት ወጪ ከማድረጋቸው በፊት ጋብቻው እንዲሰረዝ መደረጉንም ተናግረዋል።
"መምህራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋብቻው እንዲራዘም በማድረግ ትልቁን ኃላፊነት ተወጥተዋል" ብለዋል።
"ህጻናቱ በወላጆቻችው ግፊት እንዲያገቡ የተገደዱ ናቸው" ያሉት አማካሪው፣ ከህጻናቱ መካከል ለመምህሮቻቸው በመንገር ጋብቻቸው እንዲሰረዝ ጥረት ያደረጉ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በዞኑ በኣስገደ ጽምብላ ወረዳ የብርሃን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ መሰረት በየነ "በ15 ዓመቴ ወላጆቼ እንደሚድሩኝ ስለማውቅ ተቃውሞዬን ለአስተማሪዬ ተናግሪያለሁ" ብላለች።
መምህርት ብርዛፍ ብርሃነ በበኩላቸው ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከኃይማኖት አባቶችና ከወረዳው ሴቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን ከወላጆቿ ጋር ባደረጉት ውይይት የተማሪያቸው ጋብቻ እንዲራዘም መደረጉን አመልክተዋል።
"ተማሪዋ ጋብቻዋ እንዲራዘም በመደረጉ ትምህርቷን በአግባቡ መከታተል ችላለች" ብለዋል።
ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ጋብቻ ቢፈጽሙ ለማህበራዊ ችግሮች እንደሚጋለጡ ለተማሪዎቻቸው እያስተማሩ መሆናቸውን መምህርቷ ተናግረዋል ።
የትግራይ ክልል የቤተሰብ ሕግ ሴት ልጅ በ18 ወንድ ልጅ 22 ዓመት ካልሞላቸው ጋብቻ እንዳይፈጽሙ ይከለክላል ።