የወሰን ማስከበርና ተያያዥ ችግሮች የመንገድ ፕሮጀክቶችን ማስተጓጎላቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የወሰን ማስከበርና ተያያዥ ችግሮች የመንገድ ፕሮጀክቶችን ማስተጓጎላቸው ተገለጸ
አዳማ ጥር 25/2011 በአገሪቱ ወሰን ማስከበርና ተያያዥ ችግሮች የመንገድ ፕሮጀክቶችን ማስተጓጎላቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ባለፈው ዓመት ለወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ አራት ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ፈጽሟል።
በባለሥልጣኑ የምስራቅ ሪጅን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ምክትል ዳይሬክተር ኢንጅነር ገደፋው አስማማው ዛሬ በአዳማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ እንደገለጹት ችግሮቹ የመንገድሥራ በእቅድ እንዳይመራና በጥራት እንዳይከናወን እያደረገ ነው።
ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የካሳ ክፍያ የተፈጸመባቸው ንብረት ከመንገድ ክልል ውስጥ ፈጥኖ አለማንሳት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተጋነነ ነጠላ ዋጋ ማቅረብና አለአግባብ ለመጠቀም መሞከርም ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸውን የጠቀሱት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ በተለይ ለውሃ መሥመር የሚጠየቀው ግምት እንደሚጋነን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ሕገ ወጥ ግንባታ አለመከላከልና ተገንብተው ሲገኙም እርምጃ አለመውሰድ ሌሎች የመንገድ ሥራን የሚያስተጓጉሉ ምክንያቶች እንደሆኑም ተናግረዋል።
"ወጣቶች ተደራጅተውበታል በሚል የመንገድ ግብዓት ቦታዎችን አለማስከበርም የመንገድ ስራውን እየተፈታተነው ይገኛል" ብለዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ባጋጠመ የፀጥታ ችግር የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ከማስተጓጎሉም ባለፈ፤ በፕሮጀክቶች ንብረትና በሰው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አስረድተዋል።
"በክርክር ምክንያት የመንገድ ልማት መደናቀፍ የለበትም" ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ በአንድ ፕሮጀክት ብቻ ባለሥልጣኑ በ2 ሺህ 300 ግለሰቦች ተከሶ ፍርድ ቤት መቅረቡን አንስተዋል።
በአጠቃላይበወሰን ማስከበርና ተያያዥ ችግሮች ሳቢያ ከተጓተቱት ፕሮጀክቶች መካከል በደሌ መቱ፣ ሜጋ-ሞያሌ፣ ገለምሶ-መቻራ፣ ጅማ -ነቀምቴ፣ ሞጆ-መቂ ፕሮጀክቶችን በማሳያነት አቅርበዋል።
"ችግሩ የመንገድ ሥራው በእቅድ እንዳይመራና በጥራት እንዳይከናወን በማድረጉ የሕዝብ ቅሬታ ከማስከተሉም ባሻገር፤ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ኪሳራ እያደረሰ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
እንደ ኢንጅነር ገደፋው ገለፃ ባለስልጣኑ በ2010 በጀት ዓመት ብቻ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ አራት ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ፈጽሟል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ሴክተር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በመንገድ ፕሮጀክቶች እያጋጠሙ ያሉ ተግዳራቶችና መሰናክሎች እየጨመሩ መጥተዋል ብለዋል።
በውስን ሃብትና በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚሰሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉትን ክትትልና ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሐብታሙ ተገኝ በበኩላቸው በወሰን ማስከበር ምክንያት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም ችግር ማጋጠሙን አስታውቀዋል።
በመድረኩ ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዞንና የወረዳ መስተዳድር አካላት፣የመንገድ ሥራ ተቋራጮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።