ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድነት በመፍጠር ራሳቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድነት በመፍጠር ራሳቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባጥር 25/2011 ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደሚያራምዱት ርዕዮተ-ዓለም ተመሳሳይነት አንድነት በመፍጠር ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው።
ዶክተር አብይ አህመድ በመድረኩ 'የዴሞክራሲ ባህል በኢትዮጵያ' በሚል ርዕስ የውይይት ጽሁፍ አቅርበዋል።
በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጠንካራና ለአገር ግንባታ የሚበጅ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀስ ፓርቲዎች ያስፈልጓታል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው የበዙ ፓርቲዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ እነዚህ ፓርቲዎች "እኔ ብቻ በቂ ነኝ" ከሚል እሳቤ ወጥተው ለጋራ ዓላማ ቅድሚያ መስጠት አለባቸው ብለዋል።
ይህ እውን እንዲሆን በፖለቲካ ሜዳው የሚጫወቱ ሰዎች ራሳቸውን መግዛትና በመደመር አገር ለመገንባት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በራሱ አንድ ድርጅት ሳይሆን ግንባር መሆኑን አስታውሰው፤ ፓርቲዎቹ ሰብሰብ ለማለት ይህን አማራጭ መከተል እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ፓርቲዎቹ ወደ ሶስት ወይም አራት ቢመጡ ከመንግስት ጋር በቀላሉ በመሟገት የተሻለ ሀሳብ በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረግ እንደሚችሉም አክለዋል።
ኢህአዴግ በምርጫ ስርዓት ውስጥ፣ በምርጫ ሄደትና ውጤት ላይ በተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚቀርብበት ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፓርቲዎች ይህ እንዳይከሰት የምርጫ ቦርድ እንዲጠናከር የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
ቦርዱ ጠንካራና ታማኝ እንዲሆን በማድረግ ሚናቸውን መወጣት ከቻሉ ቀጣዩ የምርጫ ሂደት ያማረ እንደሚሆን በመጠቆም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ህዳር 2011 ዓም በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተወያዩበት ወቅትም መንግስት ቀጣይነት ያለው የፓርቲዎች መድረክ እንዲፈጠር ፍላጎት አለው ማለታቸው ይታወሳል።