ሞተር ብስክሌቶች ለትራፊክ አደጋ መጨመር ምክንያት እየሆኑ ነው

አዲስ አበባ ጥር 25/2011 በህገ-ወጥ መንገድ አገር ውስጥ የሚገቡ ሞተር ብስክሌቶችን ያለመንጃ-ፈቃድ የሚያሽከረክሩ ግለሰቦች ቁጥር መበራከት ለትራፊክ አደጋ መባባስ ምክንያት መሆኑ ተገለፀ።

ባለፉት አምስት ዓመታት በሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች ሳቢያ ከአምስት ሺህ በላይ አደጋዎች እንደደረሱና ይህም በተሽከርካሪዎች ከደረሱ አደጋዎች የሶስት በመቶ ድርሻ እንደነበረው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል።

ባለስልጣኑ ለኢዜአ እንደገለፀው በጠረፍ በኩል በየቀኑ ከ150 በላይ ሞተር ብስክሌቶች በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር ቤት ይገባሉ።

በህገ-ወጥ መንገድ የገቡት ሞተር ብስክሌቶች የሰሌዳ ቁጥር የሌላቸውና አሽከርካሪዎቻቸውም ያለመንጃ-ፈቃድ የሚያሽከረክሩ መሆናቸው የትራፊክ አደጋዎች እንዲበራከቱ ማድረጉን ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው።

ባምላክ ሰለሞን ከሶማሌ ክልል ሞተር ብስክሌት እያሽከረከረ በደረሰበት አደጋ እጁ፣ እግሩና አገጩ ላይ ጉዳት ደርሶበት በአቤት ሆስፒታል የህክምና ክትትል እያደረገ ይገኛል።

በአደጋው የደረሰበት ጉዳት በደንብ መናገር እንዳይችል ስላደረገው በአስታማሚው መሰረት ታደሰ አማካኝነት ነበር ስለአደጋው መንስኤ መረዳት የቻልነው።

ባምላክ በልምድ ባገኘው ዕውቀት ባጃጅ በመጠገን ህይወቱን እንደሚመራና ያለው ዕውቀት ሞተር ብስክሌት ለመንዳት እንደሚያስችለው ተማምኖ ያለመንጃ-ፈቃድ ሲያሽከረክር እንደነበር ይገልፃል።

ሆኖም ሞተር ብስክሌቷ ፍሬን የሚያስቸግራት በመሆኗና ባምላክም የቴክኒክ ችግሯን ሳይፈትሽ ሲያሽከረክር ከትልቅ መኪና ጋር ተጋጭቶ የትራፊክ አደጋ እንደደረሰበት ነው አስታማሚው የገለፀልን።

ችሎታና መንጃ-ፈቃድ ሳይኖረው ማንኛውም ሰው ሞተር ብስክሌት ባለማሽከርከር ራሱን ከአደጋ እንዲጠብቅም ጭምር ነው አስታማሚው መልዕክት ያስተላለፈው።

በሆስፒታሉ ህክምና እየተከታተሉ ያገኘናቸው ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አለሚቱ ጫልቺሳ ከሳምንታት በፊት ተሳፍረው ሲጓዙበት የነበረው ሞተር ብስክሌት በፍሬን ችግር በመገልበጡ የትራፊክ አደጋ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

የአምቦ አካባቢ ነዋሪዋ ወይዘሮ በአደጋው እግራቸው ሲጎዳ ከእርሳቸው በተጨማሪ አሽከርካሪው ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጉንና ባለቤታቸውና ሌላ አንድ ተሳፋሪም ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ይናገራሉ።

ሌሎች አሽከርካሪዎች የፍጥነት ወሰናቸውን ጠብቀው በመጓዝ ራሳቸውንና ኅብረተሰቡን ከአደጋ መከላከል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በሞተር ብስክሌትና ሌሎች ተሽከርካሪዎች የትራፊክ አደጋ ደርሶባቸው ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የገለፁት ደግሞ የአቤት ሆስፒታል የህሙማን ፍሰትና የህክምና ጥራት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሄኖክ ደረጀ ናቸው።

የተለያዩ አደጋዎች ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡ ታካሚዎች 50 በመቶ የሚጠጉት በመኪና አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን ነው ዶክተር ሄኖክ ያብራሩት።

በ2011 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት በሆስፒታሉ ለመታከም ከመጡት ስድስት ሺህ ታካሚዎች ውስጥ አንድ ሺህ 900 ያህሉ የመኪና አደጋ ደርሶባቸው ለህክምና የመጡ እንደሆኑ አስታውቀዋል።

ሆስፒታሉ ከተመሰረተበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ከ80 ሺህ በላይ ታካሚዎች አገልግሎት ማግኘታቸውን ያስረዱት ዶክተር ሄኖክ ከታካሚዎቹ ግማሽ ያህሉ በመኪና አደጋ የተጎዱ ናቸው ብለዋል።

ሞተር ብስክሌትን ጨምሮ በተለያዩ ተሽከርካሪዎች አደጋ ደርሶባቸው ወደሆስፒታሉ የሚመጡት ታካሚዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መሆኑንም ገልፀው በ2010 ወደሆስፒታሉ የመጡት ታካሚዎች ቁጥር በ2009 ከመጡት በ32 በመቶ ብልጫ እንዳለው ለአብነት ጠቅሰዋል።

ሆስፒታሉ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ያሉት ዶክተር ሄኖክ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ አሰጣጥን በተመለከተ ስልጠናዎችን ለተለያዩ ድርጅቶች እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ታካሚው አደጋ ከደረሰበት በአንድ ሰዓት ውስጥ ወደ ህክምና ተቋም መድረስ እንዳለበትና በህክምና “ጎልደን ሀወር” በምትባለው በዚህች ሰዓት ውስጥ አደጋ የደረሰበት ሰው እርዳታ እንዲያገኝ በማድረግ ህይወትን መታደግ የኅብረተሰቡ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ በላይ ለኢዜአ እንዳሉት በጠረፍ በኩል በየቀኑ 150 ሞተር ብስክሌቶች በህገ-ወጥ መልኩ ወደ አገር ቤት ይገባሉ።

ይህም በዓመት በህጋዊ መልኩ ኢትዮጵያ ከሚገቡት ይልቅ በህገ-ወጥ መንገድ የሚገቡት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

አብዛኛዎቹም ሰሌዳ አልባ መሆናቸውና የሚያሽከረክሩ ግለሰቦችም መንጃ-ፈቃድ የሌላቸው በመሆኑ ህገ-ወጥነትና አደጋ እንዲበራከት ምክንያት መሆናቸውን አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በ2006 ዓ.ም በሞተር ብስክሌት ሳቢያ 11 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው በ2010 ዓ.ም ቁጥሩ ወደ 123 ከፍ ብሏል።

በሞተር ብስክሌት በደረሰባቸው የትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በ2006 ዓ.ም ከነበረበት በ2010 ዓ.ም በእጥፍ መጨመሩን ነው ባለስልጣኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃን ዋቢ አድርጎ የገለፀው።

እናም ባለስልጣኑ ህገ-ወጦችን ለመቆጣጠር በየክልሉ ካሉ ከጉምሩክና ከፖሊስ አካላት ጋር በትበብር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በደቡብ ክልል በተሰራ የቅንጅት ስራም ከሁለት ሺህ በላይ ሞተር ብስክሌቶችን ህጋዊ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው በሌሎች ክልሎችም የኅብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግና የቅንጅት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።

ህገ-ወጥ ሞተር ብስክሌቶች በተበራከቱባቸው አካባቢዎች ያሉ ማዘጋጃ ቤቶች ጊዜያዊ ታፔላ በማዘጋጀት ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሄ በመስጠት እየሰሩ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ችግሩን ለመፍታት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግና የቁጥጥርና ወደ ህጋዊ መስመር የማስገባቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሃን የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በኩል ሚናቸውን እንዲወጡና ኅብረተሰቡ ራሱን ከጉዳት እንዲከላከልና ህገ-ወጦችን በማስተማር አደጋውን ለመቀነስ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።   

የኦሮሚያ፣ ደቡብና ሶማሌ ክልሎች የሞተር ብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት የተስፋፋባቸው ቦታዎች ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባም የሞተር ብስክሌቶች ቁጥር ጨምሯል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በህጋዊነት የተመዘገቡ ሞተር ብስክሌቶች ቁጥር 167 ሺህ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም