ቀጥታ፡

የፓልም ዘይት አወዛጋቢነት እልባት አላገኘም

አዲስ አበባ  ጥር 25/2011 የፓልም ተክል ዘይት አወዛጋቢነት አሁንም እልባት አላገኘም። 

በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ በስፋት የሚታየውና በብዙዎች ዘንድ "የሚረጋው" በሚል ቅጥያው የሚታወቀው የምግብ ዘይት የወገብና እግር ህመሞችን ጨምሮ የተለያዩ የጤና ችግር ይፈጥራል በሚል ቅሬታ ሲቀርብበት ይደመጣል። 

ከዚህ አስተሳሰብ በመነሳትም 'ዘይቱን ከምግብ ዝርዝራችን ውስጥ አውጥተነዋል' የሚሉ በርካቶች ናቸው።

ሆኖም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዘይቱ በራሱ የጤና ጉዳት እንደማያስከትል ባካሄደው ጥናት ማረጋገጡን ይገልፃል። 

በሌላ በኩል በዘይቱ ውስጥ ያለው ተፈጥሯዊ ያልሆነ ስብ በጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የውስጥ ደዌ እና ኢንዶክሪኖሎጂ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ሲሳይ ስርጉ ይናገራሉ።  

ከተጠቃሚው ዘንድ የሚቀርበውን ስጋትና ቅሬታ መሰረት በማድረግ ነው በጤና ሚኒስቴር ጥያቄ ለሁለት ዓመታት በዘይቱ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ጥናት በኢንስቲትዩቱ የተካሄደው። 

በኢንስቲትዩቱ የስነ-ምግብ ተባባሪ ተመራማሪ አቶ ክፍሌ ሃብቴ ለኢዜአ እንደገለፁት በጥናቱ መሰረት የፓልም ዘይት የተለየ የጤና ጉዳት አያስከትልም።

ተመራማሪው እንደሚሉት ጥናቱ የተካሄደው ከህዝብ አስተያየት በመነሳት ቢሆንም ወደ ደቡብ አፍሪካ በመላክ ጭምር የቤተ-ሙከራ ተግባር መከናወኑንና በእንስሳት ላይ መሞከሩንም ተናግረዋል።

በውጤቱ መሰረትም  ዘይቱን መመገብ ሙሉ በሙሉ ለጉዳት የሚዳርግ አለመሆኑን፤ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚፈጠረው የጤና ስጋትም መሰረት እንደሌለው ተረጋግጧል። 

ሆኖም ዘይቱን እጅግ አዘውትሮ ከመጠቀም ፈሳሽ ዘይቶችን እያፈራረቁ መጠቀም የሚጠቅም መሆኑንም ተመራማሪው ያነሳሉ። 

ከፍተኛ ሙቀት ለሚሹና በተለይም ለሚጠበሱ ምግቦች የፓልም ዘይትን መጠቀም የበለጠ እንደሚመረጥም ነው የስነ-ምግብ ተመራማሪው አቶ ክፍሌ የሚመክሩት። 

የምግብ ደህንነትን የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዘይቱ ወደአገር ውስጥ ገብቶ ጥቅም ላይ የሚውለው ደህንነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው ይላል።

በባለስልጣኑ የምግብ አስመጪና አከፋፋይ ኢንስፔክሽን አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ፍቅሬ የፓልም ተክል ዘይት ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ምንም ዓይነት የጤና አደጋ የማያስከትል መሆኑ ከተረጋገጠ ብቻ ነው ባይ ናቸው፤ እየተደረገ ያለውም ይኸው እንደሆነ በማከል።  

በቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌና ኢንዶክሪኖሎጂ ስፔሻሊስት ዶክተር ሲሳይ ስርጉ ግን የተለየ ሀሳብ አላቸው።

ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው አንዳንድ የጤና ስጋቶች በእርግጥም ከዘይቱ ጋር የተያያዙ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን ባይቻልም የሚረጋው የፓልም ተክል ዘይት በውስጡ ያለው ስብ አምጪ ንጥረ ነገር ለልብና ተያያዥ የደም ስር ችግሮች ሊዳርግ ይችላል። 

የህክምና ባለሙያው እንደሚሉት የኢንዱስትሪ ማቀነባበር ተግባር ሂደቱን በመቀየር "ትራንስ ፋት" የሚሰኘውን የጤና ጠንቅ የሆነ ስብ መጠን መቀነስ ይቻላል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር እስከ 2023 ባለው ጊዜ በምግብ ዘይቶች ውስጥ የሚገኝ ስብ የሚወገድበትን የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ነው።

ኢትዮጵያ ከውጭ አገር የምታስገባቸው የምግብ ዘይቶች በውስጣቸው ያለው የስብ መጠን ሊያስከትል የሚችለውን የጤና ጉዳት በማጥናት ሁኔታውን ለማሻሻል የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸውም የህክምና ባለሙያው አሳስበዋል። 

የተለያዩ አገራት አስገዳጅ ህጎችንና የአሰራር ማዕቀፎችን በመተግበር በዘይቱ ውስጥ ያለውን የስብ መጠን ቀስ በቀስ መቀነስ መቻላቸው ተረጋግጧል ሲሉም ነው ዶክተር ሲሳይ የገለፁት።

እናም ዘይት የሚያመርቱ የምግብ ኢንዱስትረዎች የአመራረት ዘዬአቸውን እየቀየሩ ሲመጡ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነውን የስብ መጠን ቀስ በቀስ ወደ ዝቅተኛ ደረጃ ማውረድ እንደሚቻል ተናግረዋል። 

መንግስት በአገሪቱ የተከሰተውን የምግብ ሸቀጥ እጥረት ለመከላከል በድጎማ ወደአገር ውስጥ እያስገባቸው ካሉት ምርቶች የፓልም ዘይት ዋነኛው ነው። 

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች ሜትሪክ ቶን የፓልም ዘይት በአብዛኛው ከኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያና ሲንጋፖር ታስመጣለች። ዘይቱ ከሌሎች ዘይቶች በተነፃፃሪ በዋጋው አነስተኛ መሆኑ እንዲመረጥ ያደርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም