አሶሳ ለስምንት ወራት ሲስተዋል ከነበረ የጸጥታ ችግር ወጥታለች ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
አሶሳ ለስምንት ወራት ሲስተዋል ከነበረ የጸጥታ ችግር ወጥታለች ተባለ

አሶሳ ጥር 25/2011 የአሶሳ ከተማ ለስምንት ወራት ሲስተዋል ከነበረ የጸጥታ ችግር ወጥታ ወደ ሠላምና መረጋጋት መመለሷን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
በካማሽ ዞንም ሠላምና መረጋጋት መፈጠሩን የክልሉ መንግሥት አረጋግጧል።
በአሶሳ ከተማ በሰኔ 2010 በተከሰተ ግጭት ከ15 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፤ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረትም ወድሟል፡፡
ከግጭቱ ማግስት ጀምሮ የከተማው ነዋሪዎችና የአገር መከላከያ ሠራዊት ባደረጉት የተቀናጀ እንቅስቃሴ ከተማዋ ወደ ሰላም መመለሷን አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል፡፡
ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ አልጋነሽ ከበደ እንደሚሉት ባለፉት ስምንት ወራት በከተማዋ ሲስተዋሉ የነበሩት ግጭቶች የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ከማወክ አልፎ ስጋት ውስጥም ከተዋቸው ነበር፡፡
በተለይ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለማድረስና ለግብይት እንቸገር ነበር ይላሉ፡፡
ወጣት አሸናፊ አብርሃም በበኩሉ የከተማዋን ሰላም ለመመለስ ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ተደራጅተው የጸጥታ ኃይሎችን እንቅስቃሴ ማገዛቸውን አስታውሷል፡፡
ወጣቶች በገበያና ሕዝብ በብዛት የሚሰበስባቸውን አካባቢዎች በመጠበቅ ያከናወኑትን ጥረትም በአብነት ያሳያል፡፡
ሁሉም ለከተማዋ ጸጥታና ደህንነት መጠበቅ ከቆመ አሁን ያለው ሰላምና መረጋጋት የማይቀጥልበት ምክንያት የለም ይላል፡፡
በግጭቱ ምክንያት በተደጋጋሚ ሲዘጋ የነበረው የአሶሳ -አዲስ አበባ መንገድ መከፈቱ የአካባቢውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዲንሰራራ አድርጎታል የሚሉት ደግሞ አቶ ሐሚድ አጠይብ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡
ከተማዋ የጸጥታ ኃይሎችና ኅብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት ሠላሟን ማግኘቷም እፎይታ እንደሆነላቸው ተናግረዋል፡፡
''የከተማዋን ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ከእርስ በርስ ግጭት ወጥተን በጋራ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ መሥራት ይጠበቅብናል'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን የአሶሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን፤ በካማሽ ዞንም ሠላምና መረጋጋትና እንደተፈጠረ አስታውቀዋል፡፡

የአሶሳ- ካማሽ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በአጭር ጊዜ እንደሚጀምርም ገልጸዋል፡፡
በተለይም በካማሽ ዞን የተቋረጠውን የመንግሥት ሥራ ሙሉ ለሙሉ ለማስጀመር ከአካባቢው የተፈናቀሉ ሠራተኞች እንደሚመለሱና የተቋረጠው ደሞዛቸው እንደሚከፈልም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአሶሳ ወደ አዲስ አበባ ሆነ ወደ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚወስዱ መንገዶች ክፍት ሆነዋል ብለዋል፡፡
አሶሳ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ ከተማ ስትሆን፤50ሺህ ያህል ነዋሪዎች እንዳሏት ይገመታል።