የድሬዳዋ ወጣቶች አንድነትና ሰላማችንን እናስቀጥላለን አሉ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ወጣቶች አንድነትና ሰላማችንን እናስቀጥላለን አሉ
ድሬዳዋ ጥር 25/2011 የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ሊያለያዩቸው በሚፈልጉ አካላት ደባ ሳይበገሩ አንድነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ፡፡
በአስተዳደሩ ግጭቶችን በማነሳሳት የተሳተፉ አካላት በፍርድ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል።
ወጣቶቹ ከድሬዳዋ ጊዜያዊ የጸጥታ ኮሚቴ ጋር ትናንት በተወያዩበት ወቅት እንደተናገሩት በመካከላቸው ልዩነት ፈጥረው ሊያጋጯቸው የሚጥሩ ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ አስተዳደሩ የሚታወቅበትን ኅብረትና አንድነት ለመመለስ ይሰራሉ፡፡
በአስተዳደሩ የሚታዩትን ችግሮች በመፍታት ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን እንደሚጥሩም አመልክተዋል፡፡
የመልካ ጀብዱ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ረመዳን ሰይድ በአገር ደረጃ የመጣው ለውጥ በአስተዳደሩ ሊተገበር ይገባል ይላል።
''በዘር ፣በብሔር፣ በኃይማኖት ተለያይተን አናውቅም። አንለያይም። ሰላማችንን ተወያይተን በመመለስ አንድነታችንን እናጠናክራለን'' ያለው ወጣት መሐመድ አብዱላሂ ነው፡፡
በአስተዳደሩ እየተተገበረ ያለው የ40/40/20 የብሄር/ብሄረሰብ ውክልና ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ስላላደረገ መቀየር ይገባዋል የሚለው ወጣት ሲሳይ አየለ ነው፡፡
''ራሳችን በራሳችን አደራጅተን ለሰላማችን እንተጋለን፣ እድሉን ለወጣቱ ስጡት'' ሲልም ጥያቄውን አቅርቧል፡፡
ወጣቱ አገር ገንቢና ተረካቢ መሆኑን የሚያስታውሰው ወጣት አብዲ ኢብራሂም፣በአስተዳደሩ በቅርቡ መታየት የጀመሩት ግጭቶች የአስተዳደሩ ወጣቶች መገለጫ እንዳልሆኑ ይናገራል።
''ታቦት በጋራ አጅበን ማውጣትና ማግባት በትውልድ ቅብብሎሽ እየፈፀምን ያለነው ተግባርና ያደግንበት ነው። ኃይማኖትና ብሔር የወጣቶች ጥል መንስዔ አይደለም'' ብሏል፡፡
የድሬዳዋ ጊዜያዊ የፀጥታ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዲዬር ጄኔራል ተስፋዬ ወልደማርያም ወጣቶቹ የቀድሞውን የፍቅር፣ሰላምና አንድነት ለመመለስ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡
በአስተዳደሩ በተፈጠሩ ግጭቶች ያለጥፋታቸው የታሰሩት ተለይተው ይፈታሉ፤ ጥፋተኞች የተላለፉት ደግሞ በሕግ ይጠየቃሉ ብለዋል፡፡