ህገ ወጥ የዱር እንሰሳት አደንን ለመከላከል የነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል--የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ህገ ወጥ የዱር እንሰሳት አደንን ለመከላከል የነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል--የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አዲስ አበባ ጥር 24/2011 ህገ ወጥ የዱር እንሰሳት ንግድና አደንን ለመከላከል በፓርኮች አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
በምክር ቤቱ የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ እንዳሉት በፓርኮቹ ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማጠናከር ያስፈልጋል።
በዘርፉ እያጋጠመ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ማከናወንና ከዘርፉ ከሚገኘው ገቢ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
ህብረተሰቡ በፓርኩ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው አዳዲስ የስራ ዕድሎችን በመፍጠር ሴቶች፣ ወጣቶችንና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ መፍጠርም ያስፈልጋል ብለዋል።
የዱር እንሰሳት ህገ ወጥ አደን፣ ንግድና ዝውውርን ለመከላከል በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተጀመሩ ሥራዎችን በማካናወን ረገድ ያለው አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑንም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
ከአጋር ድርጅቶች ጋር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡ ሰፊ ንቅናቄ እንዲካሄድ በማለት ቋሚ ኮሚቴው ኣሳስቧል።
ባለስልጣኑም በቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን ምክረ ሀሳብ በመቀበል የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ አረጋግጧል።