በአስተዳደሩ የተገባላቸው ቃል ባለመሟላቱ ሕይወታቸውን ለመምራት መቸገራቸውን የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላት ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ የተገባላቸው ቃል ባለመሟላቱ ሕይወታቸውን ለመምራት መቸገራቸውን የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላት ገለጹ
ሶዶ ጥር 24/2011 ከወላይታ ዞን አስተዳደርየተገባላቸው ቃል ባለመሟላቱ ሕይወታቸውን ለመምራት መቸገራቸውን በክብር የተሰናበቱ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ተናገሩ፡፡
ከአባላቱ አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት አስተዳደሩ በሠራዊቱ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ የአገርን ዳር ድንበርና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አስከብረው ወደ ሰላማዊ ሕይወት ሲመለሱ የገባውን ቃል ጠብቆ ሊያቋቁማቸው አልቻለም።
አስተዳደሩ በዋነኝነት በተማሩባቸው የትምህርት መስኮች ቅድሚያ ሰጥቶ ለመቅጠር፣ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታና እንዲሁም ቤት ለመስጠት የገባውን ቃል ተፈጻሚ እንዳላደረገም ተናግረዋል።
ቅሬታቸውን ከዞን እስከ ወረዳ ባሉት የአስተዳደር መዋቅሮች ቢያቀርቡም፤ሰሚ ማጣታቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
በተለይ የዞኑ አስተዳደር ለጥያቄዎቻቸው ሊያነጋግራቸው ፈቃደኝነት ማጣቱ አግባብ እንዳልሆነም ይናገራሉ።
የሃምሳ አለቃ ለምቢቱ ሌጃሞ በአገር መከላከያ ሠራዊት ለ13 ዓመታት አገርና ሕዝብን አገልግለው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ከተመለሱ አራት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡
''ቃል የተገባበት ወረቀት በእጃችን ቢኖርም፤ በየሄድንበት በአግባቡ መመሪያው 'በእጃችን የለም' በሚል ሰበብ እየተንከራተትን ነው'' ሲሉ በአስተዳደሩ የተሰጣቸው ደብዳቤ ዋጋ እንዳጡበት በምሬታቸውን ይናገራሉ፡፡
የሁለት ልጆች እናት መሆናቸውን የተናገሩት የሃምሳ አለቃ ለምቢቱ፤ ደሞዝም ሆነ ሌላ መደጎሚያ በሌለበት ሁኔታ እየገጠማቸው ያለውን ችግር ለማቃለል መንግሥት በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ሻለቃ መሰለ ባሳ የተባሉ የቀድሞ መኮንን በበኩላቸው በዞኑ የሰማዕታት ቤተሰቦችንና አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት፣የሠራዊት አባላትን አደራጅተው ወደ ሥራ ለማስገባትና የሚደጋገፉበት ማህበር ከመሰረቱ 10 ወራትን እንዳስቆጠሩ ገልጸዋል፡፡
አገርን አገልግለው በልመና የተሰማሩ የሠራዊቱን አባላት ጉዳይ መንግሥት በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል፡፡
ሻለቃ ጳውሎስ ገብረ ሥላሴ በላይቤሪያ በተሰማራው ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ጨምሮ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ከ30 ዓመታት በላይ አገልግለው በክብር መሰናበታቸውን ይናገራሉ።በአስተዳደሩ የተገባላቸው ቃል ባለመከበሩ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የሚገልጹት በቅሬታ ነው፡፡
''ለአንድ ብሄርና ለአንድ ክልል ሳይሆን ለአገር እስካገለገልን ድረስ ተገቢ ጥቅማ ጥቅም ሊጠበቅልን ይገባል'' ያሉት ሻለቃ ጳውሎስ፣በኑሮአቸው ከሌሎች ሰዎች አንሰው በመገኘታቸው፣መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ባለሟሟላታቸውና መብታቸው ባለመከበሩ ሞራላቸው መነካቱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የወላይታ ዞን ተቀዳሚ ዋና አሰተዳዳሪንና ምክትል ዋና አስተዳዳሪን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸውና በቢሮአቸው ስልክ ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም ፤ምላሻቸውን ለማግኘት አልተቻለም፡፡