ቀጥታ፡

በቀጣዮቹ 28 ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል

አዲስ አበባ ጥር 24/2011 በቀጣዮቹ 28 ቀናት ይኖራል ተብሎ የሚጠበቀው እርጥበት ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ከዛሬ ጥር 24 እስከ የካቲት 21 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይኖራል ተብሎ ስለሚጠበቀው የአየር ጠባይ አዝማሚያ ያለውን ትንበያ አስቀምጧል።

በ28 ቀናቶች ውስጥ በመደበኛ ሁኔታ ከበልግ ዝናብ መጀመር ጋር ተያይዞ የበልግ አብቃይ አካባቢ የተሻለ እርጥበት የሚያገኙበትና የማሳ ዝግጅት የሚያደርጉበት እንደሆነ ተገልጿል።

በተለይም በተጠቀሱት ቀናት መጨረሻ ላይ የበልግ ሰብሎችን መዝራት እንደሚጀምሩም በመግለጫው ተጠቅሷል።

በተሰጠው የአየር ትንበያ ሁኔታ መሰረት በአብዛኛዎቹ የበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የእርጥበት ሁኔታው ቀስ በቀስ መሻሻል ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል።

ይህም ሁኔታ ለግብርናው እንቅስቃሴ በጎ ጎን ያለውና ይህንኑ በመገንዘብ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ኤጀንሲው የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያው ላይ ገልጿል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚሻሻል የሚጠበቀው እርጥበት ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ እቅርቦት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለጫው ተመላክቷል።

በ28 ቀናቶች ውስጥ በባሮ አኮቦ ደቡባዊና ምስራቃዊ ክፍል፣ በአባይ ወንዝ፣ የላይኛው ተከዜና የላይኛው ዋቢ ሸበሌ አዋሳኝ ተፋሰሶች ላይ ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖርም ይጠበቃል።

በእነዚህ ተፋሰሶች ላይ አልፎ አልፎ የሚገኘው አነስተኛ እርጥበት ደረቅ ሁኔታ እንዳይባባስ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና በተቀሩት የኢትዮጵያ ተፋሰሶች በአመዛኙ ደረቅ ሆነው እንደሚሰነብቱ ኤጀንሲው አስታውቋል።

በተጠቀሰው ጊዜ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እየተጠናከሩ ከመሄዳቸው ጋር ተያይዞ የደቡብ ምዕራብ፣ የደቡብ፣ የሰሜን ምስራቅ፣ የምስራቅ፣ የመካከለኛውና የአጎራባች የስምጥ ሸለቆ ስፍራዎች የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም