የቀድሞው አፈ-ጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ የቀብር ስነ-ስርዓት እሁድ ይፈጸማል - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞው አፈ-ጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ የቀብር ስነ-ስርዓት እሁድ ይፈጸማል
አዲስ አበባ ጥር 24/2011 የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የአምባሳደር ዳዊት ዮሐንስ የቀብር ስነ-ስርዓት እሁድ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስተያን እንደሚፈጸም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
አስከሬናቸው ዛሬ ከአሜሪካ ኒውዮርክ አሸኛኘት ተደርጎለት ነገ ምሽት አዲስ አበባ እንደሚገባ ታውቋል።
ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የቀብር ሥነ-ስርዓታቸውም እሁድ ጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን እንደሚፈጸም አስታውቋል።
በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አቶ ዳዊት ዮሐንስ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ።
አቶ ዳዊት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት መጽደቁን ተከትሎ የመጀመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ በመሆን ከ1988 እስከ 1998 ዓ.ም አገልግለዋል።
የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በአሜሪካው ጆርጅ ታውንና በኔዘርላንድስ አምስተርዳም ዩኒቨርሲቲዎች ተከታትለዋል።
የጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳዊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም በሰሩበት ወቅት በደቡብ ሱዳን የሠላም ግንባታ፣ በቻይናና አፍሪካ ግንኙነት፣ በሠላም ማስከበርና በሌሎች ርዕሰ-ጉዳዮች ጥናቶች አካሂደዋል።