መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ-ምግባርን በመጠበቅ ለሰላም እንዲሰሩ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ-ምግባርን በመጠበቅ ለሰላም እንዲሰሩ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ጥር 24/2011መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ-ምግባርን መሰረት በማድረግ ለአገር ሰላም እንዲሰሩ የሰላም ሚኒስቴር ጠየቀ።
የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስተር ዘርፍ ማህበር እና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ 'የሰላም መገናኛ ብዙሃን ህብረት ትስስር' ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት ትናንት ማምሻውን አካሂደዋል።
በውይይት መድረኩ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ''ያለ ሚዲያ ጠንካራ ተሳትፎ የዘላቂ ሰላም ስራ አይታሰብም" ሲሉ ተናግረው፤ የሰላም ሚኒስቴር የተሰጠውን ተልእኮ ከመገናኛ ብዙሃን ተሳትፎ ውጪ ማሳካት እንደማይችል ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በትብብር ሲሰሩ ነጻነቱንና ሙያዊ ስነ-ምግባርን በጠበቀ መልኩ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በመገናኛ ብዙሃን ካልታገዘ ውጤት ሊያመጣ እንደማይችልም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ያለንን አገራዊ እሴት በማስፋት ሰላምን ለማረጋገጥ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አመልክተዋል።
መገናኛ ብዙሃን በሰላምም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ተከታታይ ሳይሆን አጀንዳዎች በመቅረጽ በቀዳሚነት መስራት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።
የመገናኛ ብዙሃን ተፈጥሯዊ ባህሪ ሰላም መሆን እንዳለበት ያሳሰቡት ሚኒስትሯ የግጭት ጉዳዮችን ሲዘግቡ ግጭቱን በሚያባብስ መንገድ ሳይሆን ማርገብ፤ ብሎም ማስወገድ በሚቻልበት ስልት ላይ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
ሰላምን ከመስበክ ጎን ለጎን ግጭት የሚያስከትሉ ጉዳዮች እንዲፈቱ የቅድመ መከላከል የመገናኛ ብዙሃን ተግባርም ማከናወን እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በቅርበት መስራት የፈለገው ወቅታዊ የሆነውን ችግር ለማርገብ ብቻ ሳይሆን አገርን ለመገንባትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በማሰብ እንደሆነ ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን ከሚኒስቴሩ ጋር ሲሰራ ነጻነቱንና ሙያዊ ስነ-ምግባሩን ጠብቆ መሆን እንደሚኖርበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት የተለያዩ የሚዲያ ሃላፊዎች በሰላም ዙሪያ በጋራ መስራት ያስፈልጋል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ከኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል በመድረኩ የተገኙት አቶ አማረ አረጋዊ ሰላምን መፍጠር የሚዲያ ግዴታ በመሆኑ ስነ-ምግባርን ጠብቆ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በጥምረት መስራት ይቻል ዘንድም ልዩነት የሚፈጥሩ አሰራርና አካሄዶችን ማስወገድና የጋራ መግባባት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
በሰላም ሚኒስቴርና በመገናኛ ብዙሃን መካከል በሚፈጠረው ትስስር በአሰራር ሂደት ላይ ልዩነት እንዳይፈጠር ለማድረግ ከወዲሁ ተግባብቶ መሄድ ተገቢ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች አቶ ሱራፍኤል ወንድሙ ሰላምን ለማረጋገጥ ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በብቃት ማሳተፍ የሰላም ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት ብለዋል።
ቀደም ሲል በልማት ጋዜጠኝነት ስም ይሰሩ የነበሩ ስራዎች አሁን ለሚታዩ ችግሮች ምክንያት እንደሆኑ አስታውሰው የሰላም ጋዜጠኝነትም ከዚህ ጋር እንዳይገናኝ ለማድረግ ተገቢ ጥንቃቄ መወሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ተተካ በቀለ በበኩላቸው የሰላም ሚኒስቴር በመገናኛ ብዙሃን እሴት የሚጨምሩ ተግባራት ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የመገናኛ ብዙሃን ትስስር ባይፈጥርም በአገሪቱ ሰላም ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከህዝብና ከግል መገናኛ ብዙሃን ጋር ሲሰራ ቆይቷል።