የመጀመሪያው የቮሊቦል ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ዛሬ በጎንደር ከተማ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የቮሊቦል ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ዛሬ በጎንደር ከተማ ተጀምሯል
አዲስ አበባ ጥር 24/2011 የመጀመሪያው የቮሊቦል ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ዛሬ በጎንደር ከተማ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽንና የጎንደር ከተማ አስተዳደር በጋራ ባዘጋጁት በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አምስት ክለቦች እየተካፈሉ ነው።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብሩህ ተክለኃይማኖት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በውድድሩ መክፈቻ ቀን ሁለት ጨዋታ ተካሂዶ መከላከያ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን፣ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ አዲስ አበባ ፖሊስን በተመሳሳይ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል።
በውድድሩ ላይ ሙገር ሲሚንቶና አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በውስጥ ችግር እንዲሁም ጣና ባህርዳር በበጀት ችግር እንዳማይሳተፉ ለፌዴሬሽኑ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
በውድድሩ አምስት ክለቦች ብቻ በመሳተፋቸው ወላይታ ድቻ በእጣ እንዲሁም አዲስ አበባ ፖሊስ ጥሩ ተሸናፊ በሚል ወደ ግማሽ ፍጻሜ እንዲያልፉ መደረጉን አስረድተዋል።
በዚሁ መሰረት ነገ ወላይታ ድቻ ከመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ መከላከያ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ለፍጻሜ ለማለፍ እንደሚጫወቱ ተናግረዋል።
የውድድሩ ዓላማ የክለቦችን የውድድር መድረክ በማስፋት ምርጥ ስፖርተኞች ለማፍራትና ስፖርቱ በቀደምት ዓመታት የስፖርቱ እድገት ይታይበት የነበረውና በአሁኑ ሰዓት የስፖርቱ እንቅስቃሴ የተዳከመበትን የጎንደር ከተማ ወደ ቀድሞው ዝና ለመመለስ የታሰበ እንደሆነ አስረድተዋል።
''ፌዴሬሽኑ ውድድሮች በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች በማስቀጠል ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል'' ብለዋል።
በውድድሩ መክፈቻ ስነ ስርአት የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽንና የጎንደር ከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የቮሊቦል ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር እስከ ጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።
የቮሊቦል ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ የገባው አገሪቷ ዘመናዊ ትምህርትን ማስፋፋት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀምር በአብዛኛው በውጭ መምህራን ስለነበር መምህራኑ ስፖርቱንም እንዳስጀመሩት በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች ያሳያሉ።
የስፖርቱ መዘውተር በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን እንዲመሰረት አስችሏል።
ከ1980ዎቹ በኋላ መጠነኛ መቀዛቀዝ ያሳየው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ስፖርት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ቀድሞ ደረጃው ለመመለስ በሁለቱም ጾታ የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ማካሄድን ጨምሮ የተለያዩ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።