የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ጥር 24/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ከረፋዱ አምስት ሰአት የሚያስተናግድበት መርሃ ግብር ነገ በሊጉ የሚካሄድ ብቸኛ ጨዋታ ነው።
ከነገ በስቲያ አራት ጨዋታዎች የሚካሄዱ ይሆናል።
በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የአምናው የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከመከላከያ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው ወቅታዊ ብቃት አንጻር ተጠባቂ ሆኗል።
ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እስካሁን ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎችን ያሸነፈ ሲሆን መከላከያ ደግሞ ሁለት አሸንፎ አንድ ጊዜ ተሸንፏል።
በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ያደረጋቸቸውን ሶስት ጨዋታዎች ያሸነፈው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከረፋዱ 4 ሰአት ከ30 ቡታጅራ ከተማን ያስተናግዳል።
ቡታጅራ ከተማ ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፈ ሲሆን በሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር ሊያደረግው የነበረው ጨዋታ ቡታጅራ ከተማ በጀት ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ ሳይካሄድ ቀርቷል።
ይሁን እንጂ ቡታጅራ ከተማ ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ ባለመሆኑ የፌዴሬሽኑ የውድድርና ስነ ስርአት ኮሚቴ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በፎርፌ እንዲያሸንፍ መወሰኑ ይታወቃል።
በክልል ከተሞች መቐለ ላይ መቐለ ሰብአ እንደርታ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማና መቐለ ሰብዓ እንደርታ በተመሳሳይ 6 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከትል ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ቡታጅራ ከተማ የመጨረሻውን አስረኛ ደረጃ ይዟል።
በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 10 ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ ቡታጅራ ከተማ የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል።