ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ህገወጥ መድኃኒቶችን አስወገደ

አዳማ ጥር 24/2011 የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን 22 ነጥብ 78 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ህገወጥ መድኃኒቶች እንዲወገዱ ማድረጉን አስታወቀ።

ባለፉት ስድስት ወራት በጤና አገልግሎት ግብአቶች ላይ ቁጥጥርና ፍተሻ ተደርጎ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ መድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሳርያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉም ተመልክቷል።

በባለስልጡኑ የፕሮጀክትና ፕላን ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ዓለም እሼቴ እንዳሉት መስፈርቱን ያላሟሉና ህገ ወጥ የሆኑ መድኃኒቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉና በአግባቡ እንዲወገዱ የተደረገው ባለፉት ስድስት ወራት ነው።

መደኃኒቶቹ የተያዙት በመውጫና መግቢያ ኬላዎች ላይ በተደረገ የቤተሙከራ ፍተሻ እንዲሁም በኦዲቲንግ ኢንስፔክሽን ወቅት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከውጭ ሀገር የሚገቡ መድኃኒቶችን ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነታቸውን ለማረጋገጥ ባለስልጣኑ ከዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካለት ጋር በመተባበር የቁጥጥር ሥራ ማከናወኑንም ገልጸዋል።

በቶጎ ውጫሌ፣ ሞያሌ፣ ቃሊቲ፣ መተማና ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባለስልጣኑ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዓለም አንዳሉት በግማሽ በጀት ዓመቱ የምግብ ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር ውጤታማነትን ለማሻሻል በተደረገው እንቅስቃሴም 2ሺህ 389 ሜትሪክ ቶን ዱቄት፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተርና የምግብ ጥሬ እቃ ተይዟል።

"በተደረገ ፍተሻም ምግብና ጥሬ እቃው የመጠቀሚያ ጊዜው በመቃረቡ፣ አምራች ካምፓኒው ባለመታወቁ፣ በጉዞ ወቅት በደረሰ ጉዳትና በነቀዝ በመባላቱ ምክንያት ወደመጣበት አገር እንዲመለስ ተደርጓል" ብለዋል።

በተጨማሪም ከ200 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ፓስታ፣ ዱቄት፣ ዘይት፣ ብስኩት፣ ጁስ፣ ሩዝ፣ ወተት፣ ፍራፍሬና የምግብ ጥሬ እቃዎች በተለያየ ምክንያት በመበላሸታቸውና አስፈላጊውን መስፈርት ያላሟሉ ሆነው በመገኘታቸው ከንግድ ተቋማት ውስጥ ተሰብስበው እንዲወገዱ መደረጉን ነው ያስረዱት።

ዘይት፣ ጨው፣ የዱቄት ወተት፣ ጁስና ሌሎች 15 አይነት የምግብ ናሙናዎች ላይ በተካሄደ የቤተሙከራ ምርመራ ሰባቱ መስፈርቱን ሳያማሉ በመቅረታቸው ምርቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ መደረጉን አስረድተዋል።

"በመንፈቅ ዓመቱ በጤና አገልግሎት ግብአቶች ላይ ቁጥጥርና ፍተሻ ተደርጎም 4 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጋል" ብለዋል። 

ዋጋቸው ከ457 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የውበትና የንጽህና መጠበቅያ ምርቶችም ቁጥጥርና ፍተሻ ተደርጎላቸው ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል። 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው ህገ-ወጥ የጤና አገልግሎትና ግብአቶችን ለመቆጣጠር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ  በስሩ ስድስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችንና 17 የመውጫና  መግቢያ ኬላዎችን በማደራጀት እየሰራ ይገኛል።

በየደረጃው በሚደረጉ የቁጥጥር ሥራዎች ህዝቡን ተሳታፊ ለማድረግ በተለያዩ የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች ላይ ህዝብን የማስገንዘብ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በእዚህም ህገ ወጥ የምግብና የመድኃኒት ንግድን እንዴት መከላከል እንደሚቻልና በዘርፉ ቁጥጥር አለማድረግም በሀገር ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ህብረተሰቡ እንዲገነዘበው የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመለክተዋል።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት በቁጥጥር ሥራው ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የምግብ ቤተሙከራ አለመጠናከር፣ የባለሙያዎች አቅም ውስንነት፣ የባለድርሻ አካላትና የህዝብ ክንፉ ተሳትፎ የተደራጀና የተቀናጀ አለመሆን ይጠቀሳሉ።

ይህንን ችግር ለማቃለል የባለስልጣኑን አዋጅ የመከለስ ሥራ እየተጠናቀቀ ሲሆን ከምግብና መድኃኒት ጋር የተጣጣመ የአደረጃጀት ትግበራ፣ የሰው ኃይል ድልድልና የህግ ማዕቀፎች ዝግጀት መደረጉንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም